“ራሳችሁን የምትገዙ ሁኑ፤ ንቁም፤ ጠላታችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን በመፈለግ እንደሚያገሣ አንበሳ ወዲያ ወዲህ ይዞራል። በዓለም ዙሪያ ያሉት ወንድሞቻችሁ ተመሳሳይ መከራ እንደሚቀበሉ ዐውቃችሁ በእምነት ጸንታችሁ ተቃወሙት ” (1ኛ ጴጥሮስ 5፥8–9)።
ሁለቱ ታላላቅ የነፍሳችን ጠላቶች ኃጢአትና ሰይጣን ናቸው። ከሁሉ የከፋው ጠላት ግን ኃጢአት ነው። ምክንያቱም ሰይጣን ሊያጠፋን የሚችለው ኃጢአት እንድንሠራ በማድረግ እና ንስሐ እንዳንገባ በመከልከል ነው። እኛን የሚያጠፋን ንስሓ ያልተገባበትና ይቅር ያልተባለ ኃጢአት ብቻ ነው። ሰይጣን አይደለም።
እግዚአብሔር እስከፈቀደለት ድረስ ሰይጣን በሕይወታችን ክፋትን ሊያመጣ ይችላል። የታሰረበትን ገመድ እስከለቀቀለት ርቀት ድረስ ሊያጠቃን ይችላል። ኢዮብ ላይ እንዳደረገው ሊጎዳን፣ ከፍ ሲልም በሰምርኔስ ቅዱሳን ላይ እንዳደረገው ሊገድለን ይችላል (ራዕይ 2፥10)። ነገር ግን ሰይጣን ሊኮንነን ወይም የዘላለምን ሕይወታችንን ሊነጥቀን አይችልም። የመጨረሻውን ጉዳት ሊያደርስብን የሚችለው ኃጢአትን እንድንሰራ ተጽዕኖ በማድረግ እና ከንስሓ እንድንርቅ በማታለል ነው። ሌላ ዓላማ የለውም፤ ሐሳቡ እና ውጥኑ ሁሉ ይህንን ለማሳካት ነው።
ስለዚህ የሰይጣን ዋና ስራው ለኃጢአት ያለንን ዝንባሌ ማበረታታት፣ ማሟሟቅ፣ መርዳት እና መውደቃችንን ማረጋገጥ ነው። ይህንን በማድረግ ከእምነትና ከንስሐ ያርቀናል።
በኤፌሶን 2፥1-2 ላይ በግልጽ ተቀምጦልናል፦ “በበደላችሁና በኃጢአታችሁ ሙታን ነበራችሁ … በአየር ላሉት መንፈሳዊያን ኅይላት ገዥ ለሆነውና አሁንም ለእግዚአብሔር በማይታዘዙት ሰዎች ላይ ለሚሠራው መንፈስ እየታዘዛችሁ ትኖሩ ነበር” ይለናል። “ኃጢአት መሥራት” ማለት በዓለም ላይ ካለው የሰይጣን ኃይል ጋር መስማማት ነው። ሰይጣን የግብረገብ ውድቀትን ሲያመጣ፣ የሚያመጣው በኃጢአት በኩል ነው። ኃጢአት ስንሠራ በእርሱ አጥርና ክልል ውስጥ እንንቀሳቀሳለን፤ ከእርሱም ጋር እንተባበራለን። ኃጢአት ስንሠራ ለዲያብሎስ ቦታንና እድል ፈንታን እንሰጣለን (ኤፌሶን 4፥27)።
በፍርድ ቀን የሚኮንነን ብቸኛው ነገር ንስሓ ያልተገባበትና ይቅር ያልተባለ ኃጢአት ነው። በሽታ፣ መከራ፣ ስደት፣ ዛቻ፣ ቅዠት፣ ወይም አጋንንት አይደለም መጥፊያችን። ሰይጣን ደግሞ ይህን ያውቃል። ስለዚህ፣ ምንም እንኳ በርካታ አጋንንታዊ ስራዎች ቢሰራም፣ ዋና ትኩረቱ ክርስቲያኖችን ግር በሚሉ ሰይጣናዊ አሠራሮች ማስፈራራት ሳይሆን፣ በክፋት እና በኀጢአት አስተሳሰብ ልባቸውን ማርከስ ነው።
ሰይጣን ሊይዘንና ሊያጠቃን የሚፈልገው እምነታችን በደከመበትና ለጥቃት በተጋለጠበት ወቅት ነው። በዋናነት ሊያጠቃ የሚፈልገው ጥቃቱን የምንቃወምበትን መሳሪያችንን መሆኑ ደግሞ ግልጽ ነው። ለዚህ ነው ጴጥሮስ “በእምነት ጸንታችሁ ተቃወሙት” የሚለን (1ኛ ጴጥሮስ 5፥9)። ጳውሎስም “የሚንበለበሉትን የክፉውን ፍላጻዎች ሁሉ ልታጠፉ የምትችሉበትን … የእምነት ጋሻ አንሱ” ያለው ለዚህ ነው (ኤፌሶን 6፥16)።
የዲያብሎስን ስራ የማጨናገፊያው መንገድ፣ እርሱ ከምንም በላይ ሊያጠፋው የሚፈልገውን እምነታችንን አብዝተን ማጠንከር ነው።