ትተውት የወጡትን አገር ቢያስቡ ኖሮ፣ ወደዚያ የመመለስ ዕድል ነበራቸው። አሁን ግን ከዚህ የሚበልጠውን ሰማያዊ አገር ይናፍቃሉ። (ዕብራውያን 11፥15-16)
እምነት እግዚአብሔር የሰጠውን ተስፋ ይመለከታል፤ ከልቡም ይፈልገዋል። “ከዚህ የሚበልጠውን ሰማያዊ አገር ይናፍቃሉ።” እስቲ ለአፍታ በዚህ ሐሳብ ላይ ቆዩ።
ብዙ ሰዎች የሚያድን እምነትን (Saving Faith) በአንድ ሰው ፍላጎቶች እና መሻቶች ላይ ለውጥ የማያመጣ ተራ ውሳኔ አድርገው ያሳንሱታል። ነገር ግን በታላቁ የእምነት ምዕራፍ የሆነው ዕብራውያን 11 ውስጥ ያለው የዚህ ክፍል ዋና ሃሳብ፣ በእምነት መኖርና መሞት ማለት የአዲስ ፍላጎቶችና እርካታዎች መኖር ነው የሚል ነው። በሚያድን እምነት ዳግመኛ የተወለደ ሰው አዳዲስ ፍላጎቶች እና እርካታዎች ይኖሩታል።
ቁጥር 14፣ ስለእምነታቸው የተነገረላቸው በዕብራውያን 11 ላይ ያሉት የቀደሙት ቅዱሳን፣ ይህ ዓለም ከሚሰጠው የተሻለ አገርን ይፈልጉ እንደነበር ይናገራል። ቁጥር 16 ደግሞ፣ የዚህ ምድር ሕይወት ከሚሰጠው የተሻለ ነገርን ይሹ ነበር ይለናል። “የሚበልጠውን ሰማያዊ አገር ይናፍቃሉ።”
በእግዚአብሔር በጣም ከመማረካቸው የተነሣ፣ ከእግዚአብሔር ጋር ከመሆን በላይ የሚያረካቸው ነገር አልነበረም።
ስለዚህም፣ የሚያድን እምነት ይህ ነው፦ የእግዚአብሔርን ተስፋዎች ከሩቅ በማየት፣ ዋጋ የምንሰጠውን ነገር መለወጥ እና ዓለም ከሚሰጠው በላይ የእግዚአብሔርን ተስፋዎች ማመን፣ መፈልግ እና መሻት ነው።