የዳንበት እምነት ይቅርታን ይወዳል | ሐምሌ 7

እግዚአብሔር በክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ፣ እናንተም ይቅር ተባባሉ፤ እርስ በርሳችሁ ቸሮችና ርኅሩኆች ሁኑ።” (ኤፌሶን 4፥32)

የሚያድን እምነት ማለት ይቅር መባላችንን ማመን ማለት ብቻ አይደለም። ይልቁንም ይህ እምነት የኅጢአትን አስከፊነት እና የእግዚአብሔርን ቅድስና ይመለከታል፤ ደግሞም የእግዚአብሔርን ይቅርታ ሊገለጽ በማይችል መልኩ ክቡር እና ውብ መሆኑን በመንፈስ ይገነዘባል። ዝም ብለን መቀበል ብቻ ሳይሆን እንደነቅበታለን። ይቅር ባይ ከሆነው ታላቁ እግዚአብሔር ጋር ባለን አዲስ ወዳጅነት እንረካለን፣ ደስም እንሰኝበታለን።

በእግዚአብሔር ይቅርታ ማመን ማለት እኔ ነጻ እንደወጣሁና ይቅር እንደተባልኩ ከመቀበል ያልፋል። የእግዚአብሔር ምሕረት በአጽናፈ ዓለሙ ሁሉ ውስጥ የከበረው እውነት ነው። በዓለም ላይ ያለው እጅግ ጣፋጩ እውነት እግዚአብሔር እኛን ይቅር የማለቱ ዜና ነው። ይህን ዜና ከማጣጣም የላቀ ውድ እውነት የለም። የሚያድን እምነት በእግዚአብሔር ይቅር መባልን ዋጋ ይሰጣል፤ ከዚህም በመነሳት ይቅር ባዩን እግዚአብሔርንና በክርስቶስ ለእኛ ያደረገልንን ሁሉ ማክበርና ዋጋ መስጠት ይጀምራል። ይህ ተሞክሮና ልምምድ ይቅር ባይ ሕዝቦች በመሆናችን ላይ ትልቅ አስተዋጽኦ አለው።

ይቅርታችን የተገዛበት ታላቁ ድርጊት የተከናወነው ያኔ ገና ክርስቶስ መስቀል ላይ ሲሞት ነው። ይህን የተደረገልንን ወደ ኃላ በማየት ሁልጊዜ የምንቆምበትን ጸጋ እናስተውላለን (ሮሜ 5፥2)። በዚህም በእርሱ ዘንድ እኛ አሁንና ወደፊት ሁልጊዜም እንደተወደድንና ተቀባይነትን እንዳገኝን እንረዳለን። ሕያው የሆነው እግዚአብሔር ይቅር ባይ እንደሆነ እንማራለን።

ነገር ግን ይህ ይቅር መባላችንን የምንለማመድበት ታላቁ ተግባር ለአሁን ብቻ ሳይሆን ለወደፊቱም ለዘላለም የሚቀጥል ነው። ይቅር ባይ ከሆነው ታላቁ እግዚአብሔር ጋር ያለን አስደሳቹ ኅብረት ለዘላለም ይኖራል። ስለዚህም ይቅር የማለት ነፃነት፣ ፍላጎቶችን ሁሉ ከሚያረካው ከይቅር ባዩ አምላክ ጋር ከሚደረግ ኅብረት ይመነጫል።

እምነታችን የተንጠለጠለው በቀላሉ ወደ መስቀሉ ተመልክተን ከዕዳ ነጻ መውጣታችንን በማሰብ ላይ ብቻ ከሆነ፣ ቂመኞች ሆነን ልንቀጥል እንደምንችል ተምሬአለሁ። የእውነተኛ እምነት ምንነት ግን ከዚህ የጠለቀ እና የጠነከረ ትርጉም አለው። በእውነተኛ እምነት መዳን ማለት ከቅጣት ማምለጥ ማለት ብቻ ሳይሆን፣ እግዚአብሔር በኢየሱስ በኩል ለእኛ በሆነው ነገር ሁሉ ጥልቅ እርካታ ማግኘትም ጭምር ነው።

ይህ እምነት ወደ ኋላ የሚመለከተው እኛ ነጻ መውጣታችንን ለማወቅ ብቻ አይደለም፤ ይልቁንም ከእርሱ ጋር ኅብረት የምናደርግባቸውን ማለቂያ የሌላቸውን የታረቁ ነገዎቻችን ያቀረበልንን እግዚአብሔርን ለማየትና ለማጣጣም ነው። ይቅር ባይ ከሆነው አምላክ ጋር እንዲህ አይነት እርካታን የተሞላ ኅብረት ማድረጋችን፣ ይቅር ባይ ሕዝብ ለመሆናችን ወሳኝ ሚና አለው።