እግዚአብሔርን በጥማችሁ አገልግሉት | ሰኔ 18

ስለዚህ በሥጋ ብንኖርም ወይም ከሥጋ ብንለይም ዐላማችን እርሱን ደስ ማሰኘት ነው። (2ኛ ቆሮንቶስ 5፥9)

ሕይወታችሁን በሙሉ እግዚአብሔርን ለማስደሰት ስትጥሩ ኖራችሁ፣ ለካ ስታደርጉ የነበረው ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት አስጸያፊ እንደሆነ ብታውቁ ምን ትላላችሁ? ልክ ፈሪሳውያኑ እንደሆነባቸው ማለት ነው (ሉቃስ 16፥14-15)።

ምናልባት አንድ ሰው፣ “ይህማ አይሆንም፤ እግዚአብሔር እርሱን ለማስደሰት የሚሞክርን ሰው አይጥልም” ብሎ ሊመልስ ይችላል። እንዲህ የሚለው ሰው ግን ያደረገውን አያችሁ? ራሱ ስለ እግዚአብሔር በሚያስበው እና ‘እግዚአብሔር እንዲህ ነው’ ብሎ በሳለው ነገር ላይ ተንተርሶ ነው እዚህ ድምዳሜ ላይ የደረሰው። ለዚህ ነው በቅዱሳት መጻሕፍት በተገለጠው የእግዚአብሔር ባሕርይ መጀመር ያለብን።

እግዚአብሔር በተራራ ላይ እንደሚገኝ ምንጭ እንጂ እንደ በርሜል ውሃ አይደለም። የተራራ ምንጭ በራሱ ይሞላል። ያለማቋረጥ በመፍሰስ ለሌሎችም ይገብራል። የበርሜል ውሃ ግን በቧንቧ ወይም በባልዲ መሞላት ያስፈልገዋል። ስለዚህ፣ ትልቁ ጥያቄ ይህ ነው፦ የተራራ ምንጭን እንዴት ማገልገል ይቻላል? በርሜልስ እንዴት ይገለገላል? እግዚአብሔርን እንደ እግዚአብሔርነቱ እንዴት ማክበር ይቻላል?

የበርሜል ውሃ ዋጋን ማክበር ከፈለጋችሁ፣ ሙሉ፣ ንጹሕና ጠቃሚ እንዲሆን ተግታችሁ መሥራት አለባችሁ። ነገር ግን የተራራውን ምንጭ ዋጋ ማክበር ከሆነ ፍላጎታችሁ፣ በእጆቻችሁ እና በጉልበቶቻችሁ ተንበርክካችሁ ልባችሁ እስኪረካ፣ አቅም እስክታገኙ ትጠጡና፣ ሮጣችሁ በመውረድ ያገኛችሁትን ለሕዝብ ሁሉ ታውጃላችሁ። መጥተው እንዲጠጡም ትለምናላችሁ።

እርዳታ ክፉኛ እንደሚያሻው አንድ ኃጢአተኛ፣ ተስፋዬ በሙሉ የተንጠለጠለው በዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ላይ ነው፦ እግዚአብሔር ማቅረብ በምችላት አንዲት ነገር ብቻ የሚደሰት አምላክ ነው። ያለኝ አንድ ነገር ነው። እርሱም ጥማት ነው። ብቸኛው ይዤው ልመጣ የምችለው ነገር መጠማቴን ነው። የእግዚአብሔር ሉዓላዊ ነፃነት እና በራሱ በቂ መሆኑ ለእኔ ውድ ሃብት የሆኑት ለዚህ ነው፦ እግዚአብሔር የሚደሰተው፣ በተደረደሩ የውሃ ባልዲዎች ብዛት ሳይሆን፣ የጸጋውን ምንጭ ለመጠጣት በተንበረከኩ ጉልበቶች እና በተሰበሩ የኃጢአተኞች ልብ ነው። ተስፋዬም ሁሉ የተመሠረተው እዚህ እውነት ላይ ነው። 

አትሳሳቱ፣ ዛሬም ሆነ ለዘላለም በምናደርገው ነገር ሁሉ እግዚአብሔርን ማስደሰት መፈለግ አለብን። ነገር ግን መላ ሕይወታችን የተመሠረተው፣ ያስደስተዋል ብለን ባሰብነው የተሳሳተ ድርጊት ላይ ከሆነ፣ ወዮልን። ጌታ፣ ሰዎች በሚያቀርቡለት ነገር እንደሚሞላ በርሜል ሲታሰብ ደስ አይለውም። ነገር ግን እንደማያቋርጥ የእርካታ ምንጭ በሚያዩት ሰዎች ይደሰታል። እኛ ለእርሱ የምናስገባለት ነገር የለም። ከእርሱ እንቀዳለን እንጂ ወደ እርሱ አንሞላም። መዝሙር 147፥11 እንደሚለው፦”እግዚአብሔር በሚፈሩት፣ በምሕረቱ በሚታመኑትም ይደሰታል።”