ሌሎችን በማገልገል መገልገል | ጥር 24

ኢየሱስም ሐሳባቸውን ዐውቆ፣ እንዲህ አላቸው፤ “እንጀራ ስለሌለን ነው በማለት ምን ያነጋግራችኋል? አሁንም አታስተውሉምን? ልብስ አትሉምን? ወይስ ልባችሁ ደንድኖአል?” (ማርቆስ 8፥17)

ኢየሱስ አምስት ሺህ እና አራት ሺህ ሰዎችን በጥቂት እንጀራ እና ዓሣ ከመገበ በኋላ፣ ደቀ መዛሙርቱ የሚበቃቸውን እንጀራ ለራሳቸው ሳይዙ ወደ ጀልባ ገቡ።

ችግራቸውን መነጋገር ሲጀምሩም፣ ኢየሱስ፣ “እንጀራ ስለሌለን ነው በማለት ምን ያነጋግራችኋል? አሁንም አታስተውሉምን? ልብስ አትሉምን?” ይላቸዋል (ማርቆስ 8፥17)። ያላስተዋሉት ምንድን ነው?

ደቀመዛሙርቱ የትርፍራፊው ትርጉም አልገባቸውም። እነርሱ ሌሎችን ሲንከባከቡ ኢየሱስ እነርሱን እንደሚንከባከብ አላስተዋሉም።

ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፦ “አምስቱን እንጀራ ለአምስት ሺህ ሰው በቈረስሁ ጊዜ ስንት መሶብ ሙሉ ትርፍራፊ አነሣችሁ?” እነርሱም፣ “ዐሥራ ሁለት” አሉት። “ሰባቱንስ እንጀራ ለአራት ሺህ በቈረስሁ ጊዜ ስንት መሶብ ሙሉ ትርፍራፊ አነሣችሁ?” አላቸው። እነርሱም፣ “ሰባት” አሉት። እርሱም፣ “እስከ አሁን አላስተዋላችሁም ማለት ነውን?” አላቸው” (ማርቆስ 8፥19-21)።

ያላስተዋሉት ምንን ነው? ትርፍራፊን።

ትርፍራፊው ላገለገሉት ነበር። እንደውም፣ የመጀመርያው ጊዜ 12 አገልጋዮች እና 12 መሶብ ትርፍራፊ ነበር (ማርቆስ 6፥43)። አንድ ሙሉ መሶብ ለእያንዳንዱ አገልጋይ ማለት ነው። ሁለተኛው ጊዜ ደግሞ ሰባት መሶብ ነበር – ሰባት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የመትረፍረፍ እና የሙሉነት ቁጥር ነው።

ስለዚህ ያልተረዱት ይህንን ነው። ኢየሱስ ለእነርሱ ግድ እንደሚለው አላስተዋሉም ነበር። ኢየሱስን በመስጠት ልትበልጡት አትችሉም። ከእርሱ በላይ ሰጪ መሆን አይቻልም። ሕይወታችሁን ለሌሎች ስትኖሩ፣ የሚጎድላችሁ አይኖርም፤ የሚያስፈልጓችሁ ነገሮች ሁሉ ይሟላሉ። “አምላኬም እንደ ታላቅ ባለጠግነቱ መጠን የሚያስፈልጋችሁን ሁሉ በክርስቶስ ኢየሱስ ይሞላባችኋል” (ፊልጵስዩስ 4፥19)።