“በመከራችንም ሁሉ ደስታዬ ወሰን የለውም።” (2ኛ ቆሮንቶስ 7፥4)
ጳውሎስ ከሌሎች ሰዎች የሚለይበት ነገሩ ምን እንደሆነ ታውቃላቸሁ? በመከራ ውስጥ ሲያልፍ ወይም ነገሮች መልካም ሳይሆኑለት ሲቀሩ፣ የእርሱ ደስታ ግን የተጠበቀ መሆኑ ነው።
ቆይ ታዲያ ይህ ከየት የመጣ ነው?
ከሁሉም በፊት፣ ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “ሰዎች ስለ ሰው ልጅ ሲጠሏችሁ … እነሆ፤ ወሮታችሁ በሰማይ ታላቅ ነውና፣ በዚያን ቀን ደስ ይበላችሁ፤ ፈንድቁም፤” (ሉቃስ 6:22-23)። ስለ ኢየሱስ ሲባል የሚመጣ መከራና ችግር በሰማይ የሚኖራችሁን ትርፍ ዕጥፍ ድርብ ያደርገዋል። የሰማዩ ዋጋ ደግሞ ከዚህ ዓለሙ ሀብትና ሽልማት እጅግ፣ እጅግ ይበልጣል።
ሁለተኛ፣ ከአስተዳደጋችን ወይም ከአስተሳሰባችን እና ከጥረታችን ሳይሆን፣ ከመንፈስ ቅዱስ የሚመጣ ነው። “የመንፈስ ፍሬ ግን … ደስታ … ነው” (ገላትያ 5:22)። “እናንተ እኛንና ጌታን መስላችኋል፤ ምንም እንኳ ብርቱ መከራ ቢደርስባችሁም፣ ቃሉን በመንፈስ ቅዱስ ደስታ ተቀብላችኋል” (1ኛ ተሰሎንቄ 1:6)።
ሦስተኛ፣ በእግዚአብሔር መንግስት ውስጥ ተካፋይ ከመሆን የሚመጣ ነው። “የእግዚአብሔር መንግሥት ጽድቅና ሰላም፣ በመንፈስ ቅዱስም የሆነ ሐሤት ነው እንጂ፣ የመብልና የመጠጥ ጕዳይ አይደለም” (ሮሜ 14:17)።
አራተኛ፣ በእምነት በኩል — ማለትም እግዚአብሔርን ከማመን — የሚመጣ ነው። “በእርሱ በመታመናችሁ የተስፋ አምላክ ደስታንና ሰላምን ሁሉ ይሙላባችሁ” (ሮሜ 15:13)። “ይህን በማስተዋል፣ በእምነት እንድታድጉና ደስ እንዲላችሁ፣ በሁላችሁ ዘንድ እንደምቈይና እንደምኖር ተረድቻለሁ” (ፊልጵስዩስ 1:25 )።
አምስተኛ፣ ኢየሱስ ጌታ መሆኑን ከማየትና ከማወቅ የሚመጣ ነው። “ምንጊዜም በጌታ ደስ ይበላችሁ” (ፊልጵስዩስ 4:4)።
ስድስተኛ፣ በእነዚህ የደስታ ምንጮች ላይ እንድናተኩር እኛን ለማገዝ አጥብቀው ከሚተጉ አማኝ ወዳጆቻችን የሚመጣ ነው። “ደስ እንዲላችሁ ከእናንተ ጋር እንሠራለን” (2ኛ ቆሮንቶስ 1:24)።
ሰባተኛ፣ በብዙ መከራ ውስጥ ከሚወለደው ቅድስና የሚመጣ ነው። “በመከራችንም ሐሤት እናደርጋለን፤ ምክንያቱም መከራ ትዕግሥትን እንደሚያስገኝ እናውቃለን። ትዕግሥት ጽናትን፣ ጽናት የተፈተነ ባሕርይን፣ የተፈተነ ባሕርይ ተስፋን፤ …” (ሮሜ 5:3-4)
ጳውሎስ፣ “ደስታዬ ወሰን የለውም” እንዳለው እኛም ማለት ካልቻልን፣ “እኔ የክርስቶስን ምሳሌ እንደምከተል እናንተም የእኔን ተከተሉ” በማለት ጳውሎስ ያበረታታናል (1ኛ ቆሮንቶስ 11:1)። ይህ ለአብዛኞቻችን የፀሎት ጥሪ ነው። ምክንያቱም በመንፈስ ቅዱስ ደስታ የተሞላ ሕይወት መኖር በራሱ የተአምራት ሕይወት ነው።