ጥላዎች እና ምንጮች | ነሐሴ 26

የእግዚአብሔር ክብር ለዘላለም ጸንቶ ይኑር፤ እግዚአብሔር በሥራው ደስ ይበለው፤ እርሱ ምድርን ሲመለከት፣ ትንቀጠቀጣለች፤ ተራሮችም እርሱ ሲዳስሳቸው ይጤሳሉ። በሕይወት ሳለሁ ለእግዚአብሔር እዘምራለሁ፤ ቆሜ እስከ ሄድሁ ድረስም አምላኬን እወድሳለሁ። እኔ በእግዚአብሔር ደስ እንደሚለኝ፣ የልቤ ሐሳብ እርሱን ደስ ያሰኘው (መዝሙር 104፥31-34)።

የፍጥረት ሥራዎች ከራሳቸው አልፈው ወደ ራሱ ወደ እግዚአብሔር ስለሚጠቁሙን እግዚአብሔር በፍጥረት ሥራ ደስ ይሰኛል።

እግዚአብሔር በፍጥረት ሥራው እንድንገረምና እንድንደነቅ ይፈልጋል። ነገር ግን ፍጥረቱ በራሱ ግብ ሆኖ አይደለም። ይልቁንም የፍጥረትን ሥራ አይተን፣ የጣቱ ሥራዎች ብቻ (መዝሙር 8፥3) እንዲህ በጥበብ እና በኀይል፣ በግርማ እና በታላቅነት ደግሞም በውበት ከተሞላ፣ ይህ አምላክስ በራሱ ምን አይነት ይሆን በሚል አድናቆት እና ግርምት እንድንሞላ ይሻል።

እነዚህ ልክ በደብዛዛ መስታዎት እንደሚታይ የክብሩ የጀርባ ገጽታዎች ናቸው። ከዚያ ግን የፈጣሪን የራሱን ክብር ማየትስ ምን ያህል አስገራሚ ይሆን! ሥራዎቹን ብቻ ሳይሆን ራሱን! እልፍ አዕላፍ ቢሊዮን ጋላክሲዎች የሰውን ልጅ ነፍስ አያረኩም። የነፍሳችን ሙሉ እርካታ በእግዚአብሔርና በእግዚአብሔር ብቻ ነው።

ጆናታን ኤድዋርድስ የተባለው የሥነ-መለኮት ምሁር እና ሰባኪ እንዲህ ሲል ገልጾታል፦

ነፍሳችንን ሊያረካ የሚችለው ብቸኛ ደስታ በእግዚአብሔር ደስ በመሰኘት የሚገኝ ብቻ ነው። እዚህ ከሚኖረን ድንቅ ከተባለው መኖሪያ ይልቅ በመንግሥተ ሰማይ ያለውን እግዚአብሔርን በሙላት ደስ መሰኘት ፍጹም የተሻለ ነው … እነዚህ ምድራዊ ማረፊያዎች ጥላዎች ሲሆኑ ነገር ግን እግዚአብሔር ዋናው እውነተኛው አካል ነው። እነዚህ የተበታተኑ ጨረሮች ናቸው፤ እግዚአብሔር ግን የብርሃኑ ምንጭ የሆነው ፀሐይ ነው። እነዚህ ጥቃቅን ምንጮች ሲሆኑ፣ እግዚአብሔር ግን ዋናው ውቅያኖስ ነው።

ለዚህም ነው መዝሙር 104፡31-34 ትኩረቱን ሁሉ ወደ እግዚአብሔር በማዞር ምዕራፉን የሚጨርሰው። “በሕይወት ሳለሁ ለእግዚአብሔር እዘምራለሁ፤ ቆሜ እስከ ሄድሁ ድረስም አምላኬን እወድሳለሁ። እኔ በእግዚአብሔር ደስ እንደሚለኝ፣ የልቤ ሐሳብ እርሱን ደስ ያሰኘው።” በመጨረሻም ልባችንን በአድናቆት ሞልቶ እንዲትረፈረፍ የሚያደርጉትና እና አፋችንን በዘላለም ምስጋና የሚሞሉት ባሕሩ ወይም ተራራው፣ ሸለቆው ወይም ደመናዎች፣ እንዲሁም ደግሞ ታላላቅ ጋላክሲዎች ሳይሆኑ፣ እግዚአብሔር ራሱ ነው።