ኅጢአት፣ ሰይጣን፣ ሕመም፣ ወይም ፈተና | ጥቅምት 21

ይህ ነገር ከእኔ እንዲወገድልኝ፣ ጌታን ሦስት ጊዜ ለመንሁት፤ እርሱ ግን፣ “ጸጋዬ ይበቃሃል፤ ኀይሌ ፍጹም የሚሆነው በድካም ጊዜ ነውና” አለኝ። ስለዚህ የክርስቶስ ኀይል በእኔ ያድር ዘንድ፣ ይበልጥ ደስ እያለኝ በድካሜ እመካለሁ። (2ኛ ቆሮንቶስ 12፥8-9)

በክርስትያን ላይ በእምነት ምክንያት የሚመጣው መከራ በካንሰር በሽታ ከሚመጣው ስቃይ ጋር አንድ ዐይነት ነው? ለአንዱ ነገር የተገባው ተስፋ ለሌላው ይሰራል? መልሱ፣ አዎ ነው። ማንኛውም ሕይወት፣ በእምነት እና የእግዚአብሔርን ክብር በመፈለግ እስከተኖረ ድረስ፣ የተለያዩ እንቅፋቶች እና መከራዎች ይገጥሙታል። በታዛዥ ክርስትያን ላይ የሚመጣው መከራ ለእርሱ ጥሪ በመታዘዝ ምክንያት የሚከፈል ዋጋ ነው።

ክርስቶስ ባበጀልን መንገድ እርሱን ለመከተል ስንወስን፣ በሉዓላዊነቱ ስር ባለው በዚህ መንገድ ውስጥ የሚመጣውን ነገር ሁሉ ለመጋፈጥ አብረን ወስነናል ማለት ነው። ስለዚህ በካንሰር ምክንያት የአልጋ ቁራኛ ሆንን፣ ወይም ተሰደድን፣ በመታዘዝ ጎዳና የሚመጣ መከራ ሁሉ ከክርስቶስ ጋር፣ ለክርስቶስም ብለን የምንቀበለው መከራ ነው።

ደግሞም የመረጥነው ነው። ይህም ማለት በመታዘዛችን የሚመጣው መከራ በፈቃዳችን የገባንበት ነው። ስለዚህ በእግዚአብሔር ላይ አናጉረመርምም። ጳውሎስ እንዳደረገው መከራው እንዲቆም ልንፀልይ እንችላለን (2 ቆሮንቶስ 12፥8)። ነገር ግን እግዚአብሔር ከፈቀደው፣ ለመንግሥተ ሰማይ እንደሚከፈል የደቀመዝሙርነት ዋጋ እንቀበለዋለን።

በክርስትያን ታዛዥነታችን የሚገጥሙን ማንኛውም ስደት ሆነ ሕመም ወይም አደጋ አንድ የጋራ ባሕሪ አላቸው። በእግዚአብሔር መልካምነት ላይ ያለንን እምነት ለመሸርሸር ይጥራሉ፣ ከመታዘዝ መንገድም እንድንወጣ ይፈትኑናል።

ስለዚህ የትኛውም ፈተና ላይ ላይ የምንቀዳጀው የእምነት ድል እና የጸና መታዘዝ ለእግዚአብሔር መልካምነት ምስክሮች እና ለክርስቶስ ሁሉ ነገር እንደሚገባው ማሳያ ናቸው። ይህ ፈተና ሕመም፣ ሰይጣን፣ ወይም ኅጢአት ሊሆን ይችላል። ስለዚህ በክርስትና ጥሪያችን ውስጥ የምናልፍባቸው የትኞቹም መከራዎች ከክርስቶስ ጋር እንዲሁም ለክርስቶስ ስንል የሚሆኑ ናቸው።

ከእርሱ ጋር ስንል፣ መከራ ወደ እኛ የሚመጣው ከእርሱ ጋር በእምነት ስንራመድ ሲሆን፣ በመከራም መታገስ የምንችለው በድካማችን የሚራራልን ሊቀ ካህናት በሚሰጠን ጉልበት ነው (ዕብራውያን 4፥15)።

ለእርሱ ስንል ደግሞ፣ በመልካምነቱና በኅያልነቱ ላይ ያለንን እምነት መከራ ይፈትነዋል። በዚህም ውስጥ ሙሉ ካሳን መክፈል የሚችል እንደሆነ በማሳየት ከሁሉ የላቀ መሆኑን ይገልጣል።