የወጣቶች አገልግሎት ስድስት መርሆዎች

“ቤተ ክርስቲያናችሁ ለመካከለኛና ለሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ምን እየሠራች ነው?” አንድ መጋቢ ጓደኛዬ ይህን ጥያቄ በቅርቡ ጠየቀ።

ወጣቶችን በተመለከተ ልዩ ዕውቀት የለኝም። እናንተ ሳምንታዊ ዝግጅት ታዘጋጃላችሁ? ለማን? ምን ታደርጋላችሁ? ልዩ ፕሮጀክቶች ወይም ጉዞዎችስ? የተወሰነ የፕሮግራም ተለዋዋጭነት ሊኖር እንደሚችል አስባለሁ። ያን ግን ለእናንተ ልተውላችሁ።

ነገር ግን ምንም ቢሆን ምን ልንይዛቸው የሚገቡ ጥቂት መጽሐፍ ቅዱሳዊ መርሆዎች አሉ። በእኔ እይታ ብዙዎቹ የወጣት ቡድኖች እነዚህን መርሆዎች አይከተሉም።

1) በምታደርጉት ነገር ሁሉ በቤተ ክርስቲያን እና በዓለም መካከል ግልጽ የሆነ መስመር አስምሩ

ኢየሱስ፣ ጳውሎስ፣ ጴጥሮስ እና ሌሎችም አንድ ሰው ወጣትም ይሁን አዛውንት በቤተ ክርስቲያን እና በዓለም መካከል ግልጽ የሆነ መስመር ማስመር እንዳለበት አበክረው አስቀምጠዋል (ለምሳሌ፦ ማቴዎስ 18፥15-20፣ 2ኛ ቆሮ. 6፥14-7፥1፣ 1ኛ ጴጥ. 2፥9-12)። በጣም ኋላ ቀር ቢመስልም፣ እግዚአብሔር በብሉይ ኪዳን ስሙ በተጠራበት ሁሉ ላይ ልዩ የሆነ አትኩሮት ሲያደርግ እንመለከታለን። እንዲሁም በአዲስ ኪዳን፣ ኢየሱስ ስሙ ለተጠራባቸው ሁሉ ትኩረት ሰጥቷል (ለምሳሌ፦ ሕዝ. 36፥20-27፣ 36፣ ማቴ. 18፥20፣ 28፥19፣ 1ኛ ቆሮ. 5፥4)።

የወጣቶች አገልግሎት ትልቁ ፈተና በአጭሩ፦ በዓለም እና በቤተ ክርስቲያን መካከል ያለው መስመር መደብዘዝ ነው። ታውቃለህ የቤተ ክርስቲያን ልጆች እና በቤተ ክርስቲያን ያልተማሩ ልጆች ድብልቅልቅ እንዳሉህ? አንዳንዶች ክርስቲያን ነን ይላሉ፤ ሌሎች ደግሞ አይደለንም። በእውነቱ ግን ማን ልዩነቱን ሊናገር ይችላል?

እንግዲህ እውነታው ይህ ነው፤ ለዚህም ነው አንዳንድ አብያተ ክርስቲያናት በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ወጣቶችን ላለማጥመቅ የሚመርጡት። ይህ እንደ ጥሩ እርምጃ ሊታሰብ ይችላል። በዚህ አቋም ተስማማችሁም አልተስማማችሁም በቃላቶቻችሁ፣ በፕሮግራሞቻችሁ እና በተለያዩ ዘዴዎቻችሁ ወጣቶች “ቤተ ክርስቲያን እና ዓለም” የተለያዩ እንደሆኑ ማስገንዘብ ይኖርባቸዋል። በዐሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኙ ልጆቻችሁን በተሻለ መንገድ መውደዳችሁን ልታሳዩአቸው የምትችሉት ወሳኙ የሕይወታቸው ውሳኔ በመስመሩ በየትኛው በኩል መቆም እንዳለባቸው የሚወስኑት ውሳኔ እንደሆነ እንዲረዱ በማገዝ ነው።

እንዲሁም የወጣቶች አገልግሎትን የቤተ ክርስቲያን አባላት መደበኛ ኅላፊነቶች የማይተገበሩበት እንደ ቤተ ክርስቲያን የተለየ ክንፍ አድርጋችሁ አትመልከቱ። እንደዚህ ከማየት ይልቅ…

2) ታዳጊዎችን የምታጠምቁ ከሆነ እንደ አዋቂ ተመልከቷቸው

አሁንም ታዳጊዎችን አጥምቁ እያልኩ አይደለም። ማጥመቅ ይኑርባችሁ አይኑርባችሁ እርግጠኛ አይደለሁም። ነገር ግን ካደረጋችሁት (ብዙዎቻችሁ እንደምታደርጉ አውቃለሁ) እንደ አዋቂ ክርስቲያኖች ልታዩዋቸው ይገባል። በአብ፣ በወልድ፣ በመንፈስ ቅዱስ ስም ተጠምቀዋል (ማቴ. 28፥19)። ስለዚህ ከመላው ቤተ ክርስቲያን ጋር ለዚህ ስም ኅላፊነት አለባቸው (ማቴ. 18፥20፣ 1ኛ ቆሮ. 5፥4-5)። የቤተ ክርስቲያን የአካል ክፍሎች ናቸው፤ ስለዚህም አካልን ወደ መንከባከብ መሳብ አለባቸው (1ኛ ቆሮ. 12፥21-26፤ 2ኛ ቆሮ. 2፥6)።

በአባላት ስብሰባም ላይ ድምጽ ሊኖራቸው ይገባል። በንስሓ ለመመለስ ፈቃደኛ ያልሆኑበት ኃጢአት ውስጥ መኖር ከጀመሩ፣ ለቤተ ክርስቲያን ተግሣጽ (እገዳ) ተገዢ መሆን አለባቸው። በቤተ ክርስቲያኑ ዋና ስብሰባ ላይ እንዲገኙ እና ለቤተ ክርስቲያን እንዲጸልዩ ሊጠየቁም ይገባል። የጌታን እራት ከመውሰዳቸው በፊት ቅራኔዎችን እንዲቀርፉ ሊጠየቁ ይገባል። በሽማግሌዎች እይታ ሥር መሆንን እና የመሳሰሉት ነገሮች ማድረግ አለባችው።

በርግጥ እንደ አዋቂ የቤተ ክርስቲያን አባላት ኅላፊነትን እንዲወጡ መጠየቅ የክርስትና መሠረታዊ ኃላፊነቶችን እንዲወጡ እንደመጠየቅ ነው። ኢየሱስም በጎቹ ሁሉ በቤተሰብ ውስጥ ሁሉንም እንዲንከባከቡ፣ እርስ በርስ እንዲተያዩ፣ እርስ በርሳቸው በፍቅር እንዲታነጹ፣ ሰላም ፈጣሪዎች እንዲሆኑ ይፈልጋል። መጥፎ ልምዶችን በመለማመድ ወጣቱን ሌላ ነገር ማስተማር አያስፈልግም።

በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኝ ልጅን ወደ ቤተ ክርስቲያን አባልነት ማጥመቅ ማለት የወጣቶች የእምነት መግለጫ ላይ ወላጆች የሌላቸውን ሥልጣን ለቤተ ክርስቲያን መስጠት ማለት ነው። የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ወጣቶችን ሲያገለግሉ ሁልጊዜ ወላጆችን ማሳተፍ እንዳለባቸው ምንም ጥርጥር የለውም። ነገር ግን ወላጆች የተጠመቀ ልጃቸው የቤተ ክርስቲያን አባል ይሁን አይሁን የሚለውን በተመለከተ የመጨረሻ ውሳኔውን ለቤተ ክርስቲያን መተው አለባቸው። የመንግሥተ ሰማይ መክፈቻ የተሰጠው ለቤተ ክርስቲያን እንጂ ለወላጅ አይደለም (ማቴ. 16፥18-19)።

ይህ ሁሉ ነገር ታዲያ ከማጥመቃችሁ በፊት ቆም ብላችሁ እንድታስቡ ሊያደርጋችሁ ይገባል? አዎ!

3) ተጠመቁም አልተጠመቁም በእድሜ ደረጃ ከተዋቀረው የቤተ ክርስቲያን ሕይወት ጋር አዋህዷቸው

የምዕራቡ ዓለም ቢዝነስ እና ሚዲያ ለወጣቶች ገበያ ለማቅረብ እና ሸማች እንዲሆኑ ለማሰልጠን ቁጥር ስፍር የሌለውን ዶላሮችን ያወጣል፦ “ሄይ ልጆች! የምትፈልጉትን ነገር በምትፈልጉት መጠን አሁኑኑ ማግኘት ትችላላችሁ!” ለምሳሌ የዛሬዎቹ ወጣቶች ከ100 ዓመታት በፊት እንደሚያደርጉት በአዋቂዎች ዓለም ውስጥ ለመኖር ሲጥሩ በቤተ ክርስቲያን አይታዩም፤ ይልቁንም እኩዮቻቸው ከሆኑ ከብዙ ወጣቶች ጋር አብረው ጊዜ ማሳለፍን ይመርጣሉ።

አግበስባሽነት ለሌሎች ከመቆረስ ጋር ስለሚጋጭ በወጣት ፕሮግራሞቻችሁ ውስጥ የአግበስባሽነትን ሐሳብ ላለማንሸራሸር በጣም ጠንቃቃ እንድትሆኑ አበረታታለሁ። ነገር ግን የምታደርጉትን ሁሉ ወጣቶችን እውነተኛ ደቀ መዛሙርት በማድረግ ረገድ በእድሜ ደረጃ በተዋቀረው የቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ውስጥ እንዲገቡ ማድረግ የተሻለ እንደሚሠራ ይገንዘቡ። በድጋሜም  ሁሉንም የቤተ ክርስቲያን አካላት በሥራ ላይ በማየት እውነተኛው ክርስትና ምንን እንደሚወክል ይረዳሉ። ሽማግሌው ታናሹን ደቀ መዝሙር ሲያደርግ፣ ታናሹ ደግሞ ከታላቅ ሲማር ማየት ያስፈልጋቸዋል (ለምሳሌ፦ 1ኛ ጢሞ. 5፥1፤ ቲቶ 2፥2-6፤ 1ኛ ጴጥ. 5፥5)።

የክርስትና መንገድ በአረጋውያንና በወጣት ቅዱሳን መካከል ያለ አንድነት ነው፤ እናም ወጣቶቻችን በዚህ መንገድ እንዲሄዱ ከፈለጋችሁ መንገዱን አሳዩአቸው።

4) ወላጆች ወጣት ልጆቻቸውን እንዲያገለግሉ አስተምሩአቸው

መጽሐፍ ቅዱስ መጋቢዎችን ሳይሆን ወላጆችን ልጆቻቸውን በሚሄዱበት መንገድ እንዲመሩአቸው ያዛል (ለምሳሌ ኤፌ. 4፥11፣ 6፥4)። የወጣት መጋቢዎችን እናስወግድ እያልኩ አይደለም። እኔ የምለው የወጣት መጋቢዎች የእናንተ ሥራ እና ፕሮግራም ክርስቲያን ወላጆች መጽሐፍ ቅዱስን ላለመታዘዝ እንደሰበብ እንዳያስቀምጡ፣ ይልቁንም መጽሐፍ ቅዱስን እንዲታዘዙ አመቻቹላቸው።

5) በዚህ ወቅት ያለውን ወንጌልን የመስበክ እድል ተጠቀሙ

እንደ ቤተ ክርስቲያን ሽማግሌ እያንዳንዱን የአባልነት ማመልከቻ እና ሰዎች ወደ ቤተክርስቲያናችን መቀላቀላቸውን የሚናገሩትን እያንዳንዱን ምስክርነት አነባለሁ። (ይህ ለነፍሴ እንዴት ያለ ደስታ እንደሚሰጣት! )በጣም የሚያስደንቀው ደግሞ አማኝ ከሆነም ካልሆነም ቤተሰብ ይምጡ ብዙዎች ወደ ጌታ የመጡት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ላይ ነው ። ይህ ወቅት ለሰዎች ወንጌልን ለመካፈል አመቺ ወቅት ነው።

ይህ በፕሮግራማችሁ ውስጥ ምን ይመስላል? አላውቅም፤ ግን አንድ ነገር ያድርጉ!

6) 1 እስከ 5 ባሉት ነጥቦች ላይ በፕሮግራም የምታደርጉትን ሁሉ፣ ሰው ሰራሽ ዕቅዶቻችሁን በእነዚህ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ዓላማዎች ውስጥ ጣልቃ እንዲገቡ አትፍቀዱላቸው ይልቁንም አመቻቹላቸው

ያሏችሁ መዋቅሮች ወይም ቡድኖች የወጣቶቻችሁን በጉባኤ ሕይወት ውስጥ የሚያደርጉትን ተሳትፎ የሚጻረር ወይም በቤተክርስቲያን እና በዓለም መካከል ያለውን መስመር እንደማያደበዝዙ አረጋግጡ። እኩዮቻቸው ብቻ ሳይሆኑ በዕድሜ የገፉ አባላትም እንዲከታተሏቸው አድርጉ።

ይህ ሁሉ በመረሃ ግብር ደረጃ እንዴት እንደሚሠራ እርግጠኛ አይደለሁም (እስካሁን ይህን ተናግሬ ይሆን?) የእኔ ሐሳብ ግን በዚህ ጉዳይ  ላይ በደንብ ሐሳብ ማመንጨት እንዳለብን ነው። ብዙ ወላጆች “ክርስቲያን” ወጣት ልጆቻቸው ኮሌጅ ገብተው እምነታቸውን ሲተው የሚያዩት ለምን ይመስላችኋል?  የእኔ ግምት ብዙ ጊዜ በሁለት ውድቀቶች ምክንያት ነው። የደቀ መዝሙርነት ውድቀት እና በጥምቀት በአባልነት እና በተግሣጽ መዋቅራዊ ጉዳዮች ላይ ጥበብን አለመጠቀም ነው።

ታዲያ ሁለታችሁም (መጋቢዎችና ወላጆች) እንዴት በቤተ ክርስቲያን እና በዓለም መካከል ያለውን መስመር በጥንቃቄ  ታሰምራላችሁ? እንዴትስ ወንጌልን እንዲሰብኩ መርዳት ትችላላችሁ? እስኪ አንዳንድ ሐሳቦችን እንስማ!

በጆናታን ሊማን