እኛ ስላደረግነው አንዳች ነገር ሳይሆን ከዕቅዱና ከጸጋው የተነሣ ያዳነን ወደ ቅዱስ ሕይወትም የጠራን እርሱ ነው። ይህም ጸጋ ከዘላለም ዘመናት በፊት በክርስቶስ ኢየሱስ ተሰጠን (2ኛ ጢሞቴዎስ 1፥9)።
በ “ክርስቶስ ኢየሱስ” ውስጥ መሆን እጅግ የሚያስደንቅ እውነታ ነው። ከክርስቶስ ጋር መጣበቅ፣ መታሰር፣ አንድ መሆንና መተባበር አዕምሮን ሁሉ የሚያልፍ፣ ልብንም የሚሰርቅ አስደሳች ሕይወት ነው።
በክርስቶስ ከሆናችሁ ይህ ለእናንተ ምን ማለት እንደሆነ አድምጡ፦
- በክርስቶስ ኢየሱስ ዓለም ከመፈጠሩ አስቀድሞ ጸጋ ተሰጥቷችኋል። 2ኛ ጢሞቴዎስ 1፥9 “ይህም ጸጋ ከዘላለም ዘመናት በፊት በክርስቶስ ኢየሱስ ተሰጠን።”
- በክርስቶስ ኢየሱስ እግዚአብሔር ከፍጥረት በፊት መርጧችኋል። ኤፌሶን 1፥4 “[እግዚአብሔር] በፊቱ ቅዱሳንና ነውር አልባ እንድንሆን ዓለም ከመፈጠሩ አስቀድሞ በእርሱ [ክርስቶስ] መርጦናልና።”
- በክርስቶስ ኢየሱስ አማካኝነት ዘላለማዊ በሆነ ፍቅር ከቶ ከእግዚአብሔር ላትነጠሉ ተወድዳችኋል። ሮሜ 8፥38-39 “ይህን ተረድቻለሁ፤ ሞትም ይሁን ሕይወት፣ መላእክትም ይሁኑ አጋንንት፣ ያለውም ይሁን የሚመጣው፣ ወይም ማንኛውም ኀይል፣ ከፍታም ይሁን ጥልቀት፣ ወይም የትኛውም ፍጥረት፣ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ካለው ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን አይችልም።”
- በክርስቶስ ኢየሱስ ኀጢአታችሁ ሁሉ ይቅር ተብሏል። ኤፌሶን 1፥7 “በእርሱም [ክርስቶስ] እንደ እግዚአብሔር ጸጋ ባለጠግነት መጠን፣ በደሙ በተደረገ ቤዛነት፣ የኀጢአትን ይቅርታ አገኘን፤”
- በክርስቶስ ኢየሱስ በእግዚአብሔር አብ ፊት ጸድቃችኋል፤ እንዲሁም በክርስቶስ ያለው የእግዚአብሔር ጽድቅ ለእናንተ ተቆጥሮላችኋል። 2ኛ ቆሮንቶስ 5፥21 “እኛ በእርሱ ሆነን የእግዚአብሔር ጽድቅ እንድንሆን፣ ኀጢአት የሌለበትን እርሱን እግዚአብሔር ስለ እኛ ኀጢአት አደረገው።”
- በክርስቶስ ኢየሱስ አዲስ ፍጥረት እና የእግዚአብሔር ልጅ ሆናችኋል። 2ኛ ቆሮንቶስ 5፥17 “ስለዚህ ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው፤ አሮጌው ነገር ዐልፎአል፤ እነሆ፣ አዲስ ሆኗል።” ገላትያ 3፥26 “ሁላችሁም በክርስቶስ ኢየሱስ በማመን የእግዚአብሔር ልጆች ናችሁ።”
በ “ክርስቶስ ኢየሱስ” ውስጥ በመሆን የሚገኘውን ዘላለማዊ ክብርና እርካታ ከመጠማት እና በዚያም ከመደሰት መቼም እንዳትታክቱ እጸልያለሁ።