ኢየሱስ ጭንቀትን የተዋጋበት ስድስት መንገዶች | ሐምሌ 8

ከእርሱም ጋር ጴጥሮስንና ሁለቱን የዘብዴዎስ ልጆች ይዞ ሄዶ ይተክዝና ይጨነቅ ጀመር።” (ማቴዎስ 26፥37)

ኢየሱስ ከመሰቀሉ ከሰዓታት በፊት የነበረውን የነፍሱን ሁኔታ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ጭላንጭል በሚመስል አስገራሚ መንገድ ያሳየናል። ኢየሱስ ጭንቀትን እና ተስፋ መቁረጥን እንዴት ስልታዊ በሆነ መንገድ እንደተዋጋ እንመልከት።

  1. አንዳንድ የቅርብ ወዳጆችን መረጠ። “ከእርሱም ጋር ጴጥሮስንና ሁለቱን የዘብዴዎስ ልጆች ይዞ ሄዶ ይተክዝና ይጨነቅ ጀመር።” (ማቴዎስ 26፥37)
  2. የነፍሱን ገልጦ አካፈላቸው። ““ነፍሴ እስከ ሞት ድረስ እጅግ አዝናለች፤ ከእኔ ጋር በመትጋት እዚሁ ቈዩ” አላቸው።” (ማቴዎስ 26፥38)
  3. አብረውት እንዲማልዱና ከጎኑ ሆነው እንዲዋጉ ጠየቃቸው። “ከዚያም፣ “ነፍሴ እስከ ሞት ድረስ እጅግ አዝናለች፤ ከእኔ ጋር በመትጋት እዚሁ ቈዩ” አላቸው።” (ማቴዎስ 26፥38)
  4. ወደ አባቱ ልቡን አፍስሶ ጸለየ። “ጥቂት ዕልፍ ብሎ በግንባሩ በመደፋት፣ “አባቴ ሆይ፤ ቢቻል ይህ ጽዋ ከእኔ ይለፍ፤ (ማቴዎስ 26፥39)
  5. ሉዓላዊ በሆነው በአምላኩ ጥበብ ላይ ነፍሱን አሳልፎ ሰጠ። “ነገር ግን እኔ እንደምፈልገው ሳይሆን አንተ እንደምትፈልገው ይሁን” (ማቴዎስ 26፥39)
  6. ከመስቀሉ ባሻገር በሚጠብቀው ክቡር ጸጋ ላይ ዓይኖቹን ተከለ። “እርሱ በፊቱ ስላለው ደስታ መስቀሉን ታግሦ፣ የመስቀሉንም ውርደት ንቆ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጦአል።” (ዕብራውያን 12፥2)

በሕይወታችሁ አስጊ ነገር ሲከሰት ወይም ለነገ እንድትጨነቁ የሚያደርግ ፍንዳታ ሲፈነዳ፣ ይህንን አስታውሱ። በፍንዳታው ምክንያት በልባችሁ ውስጥ ድንገት የሚፈጠረው መንቀጥቀጥ ኀጢአት አይደለም። ኢየሱስም በጌቴሴማኒ ይሄው ዓይነት ስሜት ተሰምቶት ነበር። ትልቁ ችግር የሚሆነው በዚህ ድንጋጤ ከተሸነፋችሁና ተስፋ ከቆረጣችሁ ነው። ዋናው አደጋ ያለ አንዳች መንፈሳዊ ውጊያ እጅ ከሰጣችሁ ነው። ለእንደዚህ አይነቱ ኀጢአታዊ ስሜት እጅ መስጠት ደግሞ አለማመን ነው። ወደፊት ለሚጠብቀን ክብር በእምነት መዋጋት አለመቻል ነው። እግዚአብሔር በክርስቶስ ኢየሱስ በኩል የተገባልንን ተስፋዎች ሁሉ መዘንጋት ነው።

ሆኖም ግን ኢየሱስ በጌተሰማኒ ከዚህ የተለየ መንገድን አሳይቶናል። ሕመም አልባ ነው አላለንም፣ ወይም ትግል አያስፈልገውም ብሎ አልዋሸንም። የእርሱን ምሳሌ ተከተሉ። ታማኝ መንፈሳዊ ወዳጆችን ፈልጉ። የልባችሁን ግለጡላቸው። አብረዋችሁ እንዲጓዙና እንዲጸልዩላችሁ ጠይቁ። ነፍሳችሁን በእግዚአብሔር አብ ፊት አፍስሱ። በእግዚአብሔር ሉዓላዊ ጥበቡ ተደገፉ። እንዲሁም ዓይኖቻችሁን በከበረው በእግዚአብሔር ተስፋ በተዘጋጀው ደስታ ላይ አተኩሩ።