ኢየሱስ በዚህ መጽሐፍ ያልተጻፉ ሌሎች አያሌ ታምራዊ ምልክቶችን በደቀ መዛሙርቱ ፊት አድርጓል፤ ነገር ግን ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ፣ የእግዚአብሔርም ልጅ እንደሆነ ታምኑ ዘንድ፣ አምናችሁም በስሙ ሕይወት እንዲኖራችሁ ይህ ተጽፎአል።”
የዮሐንስ ወንጌል 20፥30-31
በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያደግን ብዙዎቻችን፣ እምነታችንን በተመለከተ ታላላቅ የሚባሉ ሥነ መለኮታዊ እውነታዎችን በእንቅልፍ ልባችን የማነብነብ እና የሐዋርያትን የእምነት መግለጫ እያዛጋን የመሸምደድ ብቃት አለን። ሆኖም ግን፣ በልባችን መቀጣጠል እንዲፈጠር ሊሠራ የሚገባ ታላቅ ነገር እንዳለ በጽኑ አምናለሁ። ሁሉን የፈጠረ፣ ሰማይን እና ምድርን በቃሉ ኀይል ያጸናውን፣ ታላቁን እግዚአብሔር ሙሉ በሙሉ የሚያንጸባርቀው እና ክብሩን የሚያሳየው ብቸኛው የእግዚአብሔር ልጅ ለሆነው፣ ለኢየሱስ ክርስቶስ የነበረን ፍርሀት፣ መደነቅ፣ እና አግራሞት እንደ አዲስ ሊቀጣጠል እንደሚገባ በጽኑ አምናለሁ።
እስከ ዛሬ ድረስ የተጻፉትን ተረት ተረቶች፣ ልብ አንጠልጣይ ታሪኮች፣ ስለ መናፍስት ዓለም የተጻፉ መጻሕፍት ሁሉ ብታነቡ፣ እንደ የኢየሱስ ሰው መሆን ታሪክ እጅግ በጣም አስደንጋጭ፣ ግራ የሚያጋባ፣ እንግዳ የሆነ፣ እና አዕምሮን የሚቆጣጠር ታሪክ አንድም አታገኙም።
ምንኛ ሙታን ብንሆን ነው ለእግዚአብሔር ክብር እና ታሪክ ይህን ያህል ስሜት አልባ እና ግድ የለሽ የሆንነው? በዚህ ጉዳይ ብዙ ጊዜ በእግዚአብሔር ፊት ንስሓ እገባለሁ። “እግዚአብሔር ሆይ፣ እውነተኛ ከሆነው የአንተ ታሪክ በላይ እነዚህ ታሪኮች ብዙ ጊዜ ስሜቴን ቀስቅሰዋል፤ አስገርመውኛል፤ አስደንቀውኛል፤ አስደስተውኛል። ስለዚህም ደግሞ ማረኝ!”
ምናልባት በእኛ ጊዜ የነበሩት ልብ አንጠልጣይ የጠፈር ፊልሞች ሊያደርጉልን የሚችሉት አንድ መልካም ነገር፣ ትሑታን አድርገውን በንስሓ እንድመለስ ሊረዱን ይችላሉ። ዘለዓለማዊውን እግዚአብሔር እና በግርማ የተሞላውን ክርስቶስን ስናስብ የዘነጋነውን የመደነቅ፣ የመገረምና የፍርሃት ስሜት እንደ አዲስ በልባችን ሊቀጣጠል እንደሚችል ያስታውሱን ይሆናል።
በዮሐንስ 18፥37 ላይ ያለው፣ “ስለዚህም ወደ ዓለም መጥቻለሁ” የሚለው የኢየሱስ ንግግር በሳይንስ ልብ ወለዶች ካነበባችኋቸው ዓረፍተ ነገሮች ሁሉ በበለጠ ሁኔታ እብደት የሚመስል እና ግራ የሚያጋባ ንግግር ነው።
የእግዚአብሔር መንፈስ በእኔ እና በእናንተ ላይ በኀይል እንዲሠራ፣ በልምምዶቻችን መካከል አስፈሪ በሆነ መንገድ ሰብሮ እንዲገባ እና ሊታሰብ ለማይችለው የእግዚአብሔር እውነታ ከተኛንበት እንዲቀሰቅሰን በብዙ እጸልያለሁ።
በቅርብ ቀን፣ ታላቅ መብረቅ ከፀሓይ መውጫ እስከ መጥለቂያ ድረስ ሰማዩን ሁሉ ሞልቶ፣ የ ሰው ልጅ በደመናት ከመላእክቱ ጋር ሁሉ ታጅቦ በእሳት ነበልባል ይመጣል። አስፈሪውን ክርስቶስ ያኔ በግልጽ ስናየው ወይ በታላቅ ሽብር፣ አልያም ደግሞ ጉጉት በሞላው ታላቅ መደነቅ እየተንቀጠቀጥን እንዴት ይህንን ሁሉ ጊዜ ለማዳ ከሚመስል የማይተናኮል ክርስቶስ ጋር እንደኖርን ይደንቀናል።
እነዚህን ሁሉ ነገሮች ጨምሮ መላው መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈልን፣ እንድናምንና ከደነዘዝንበት ነቅተን ወደዚህ ዓለም የመጣውን የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስን በታላቅ መደነቅ በዝግጁነት እንቀበል ዘንድ ነው።