የሚያስመካ ነገር | ሰኔ 1

በእምነት፣ በጸጋ ድናችኋልና፤ ይህም የእግዚአብሔር ስጦታ ነው እንጂ ከእናንተ አይደለም፤ ማንም እንዳይመካ በሥራ አይደለም። (ኤፌሶን 2፥8-9)

በጸጋ ብቻ በምናገኘው ነገር እንዳንመካ፣ አዲስ ኪዳን ጸጋን ከእምነት ጋር ያያይዘዋል።

ኤፌሶን 2፥8 ለዚህ ምሳሌ የሚሆን ታዋቂ ክፍል ነው። በእምነት በኩል፣ በጸጋ ብቻ። የእነዚህ ሁለት ነገሮች መገናኘት፣ የጸጋን ነጻነት ያስጠብቃል። በእምነት አማካኝነት በጸጋ ድናችኋል።

ነፍሳችን ከራሷ ባዶነት እና ከንቱነት ወደ እግዚአብሔር የተትረፈረፈ ነጻ ሙላት ዘወር የምትለው በእምነት ነው። እምነት እግዚአብሔር ላልተገባቸው ሁሉ ጸጋን በነጻ መስጠቱ ላይ ያተኩራል። ሙሉ በሙሉ የሚመሰረተው በእግዚአብሔር ችሮታ ላይ ነው።

ስለዚህ፣ እምነት በተፈጥሮው ትምክሕተኝነትን በማስወገድ ከጸጋ ጋር ይተባበራል። እምነት ከየትኛውም ሊመሰገን ከሚገባ ድርጊት ጀርባ ጸጋን ይመለከታል። ስለዚህ፣ የጸጋ ባለቤት ከሆነው ከጌታ ውጭ፣ እምነት በአንዳች አይመካም።

ስለዚህ ጳውሎስ፣ “መዳን በእምነት በኩል በጸጋ ብቻ ነው” ካለ በኋላ፣ “ይህም የእግዚአብሔር ስጦታ ነው እንጂ ከእናንተ አይደለም፤ ማንም እንዳይመካ በሥራ አይደለም” በማለት ይናገራል (ኤፌሶን 2፥8-9)። እምነት ነጻ በሆነውና በተትረፈረፈው ጸጋ ላይ ስለሚያተኩር፣ በሰው መልካምነት፣ ጥበብ ወይም ጉብዝና በፍጹም አይመካም። እምነት የሚያየው መልካም ነገር የጸጋን ፍሬ ብቻ ነው።

እምነት፣ ከእግዚአብሔር ዘንድ የሆነውን “ጥበባችን፣ ጽድቃችንና ቅድስናችን፣ [እና] ቤዛችንንም” ይመለከትና “የሚመካ በጌታ ይመካ” ይላል (1ኛ ቆሮንቶስ 1፥30-31)።