ታላቅ ጽናትና ትዕግሥት ይኖራችሁ ዘንድ፣ እንደ ክቡር ጕልበቱ መጠን በኀይል ሁሉ እየበረታችሁ፣ ደስ እየተሰኛችሁ፣ በቅዱሳን ርስት በብርሃን ተካፋዮች ለመሆን ያበቃንን አብን እንድታመሰግኑ ነው። (ቈላስይስ 1፥11)
“እየበረታችሁ” የሚለው ቃል ትክክለኛ ቃል ነው። ጳውሎስ በቈላስይስ ለምትገኘዋ ቤተክርስቲያን ሲጸልይ፣ “ታላቅ ጽናትና ትዕግሥት ይኖራችሁ ዘንድ፣ እንደ ክቡር ጕልበቱ መጠን በኀይል ሁሉ እየበረታችሁ” ብሏል (ቈላስይስ 1፥11)። ትዕግስት የውስጣዊ ብርታት መገለጫ ነው።
ችኩል ሰዎች ደካማ ናቸው። በዚህም ምክንያት በራሳቸው መቆም አይችሉም። ደካማ ልባቸውን በሚደግፉላቸው ሁኔታዎች እና ዕቅዶች ላይ ይመረኮዛሉ። ታዲያ፣ ዕቅዳቸውን የሆነ ሰው ሲያበላሽባቸው ቁጣቸው፣ ማስፈራሪያቸው እና ግሳፄያቸው ከደካማ ሰው የሚወጣ አይመስልም። ነገር ግን ይህ ሁሉ ጩኸት የድካማቸው መደበቂያ ነው። ትዕግስት ታላቅ ውስጣዊ ብርታትን ይጠይቃል።
ለክርስቲያኖች፣ ይህ ብርታት የሚመጣው ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው። ለዚህ ነው ጳውሎስ ለቈላስይስ ሰዎች የሚጸልይላቸው። እግዚአብሔር ለክርስትና ሕይወታቸው የሚያስፈልጋቸውን ጽኑ ትዕግስት እንዲሰጣቸው ይለምንላቸዋል። “የዚህ ትዕግስት ብርታት፣ ‘እንደ [እግዚአብሔር] ክቡር ጕልበቱ መጠን’ ነው” ሲል፣ አንድ ሰው ትዕግስት እንዲኖረው መለኮታዊ የሆነ ኃይል ያስፈልገዋል ማለቱ ብቻ አይደለም። ነገር ግን፣ በዚህ “ክቡር ጉልበት” ላይ ያለ እምነት፣ የትዕግስት ኃይል የሚመጣበት መንገዱም ጭምር ነው እያለ ነው።
ትዕግስት በእርግጥ የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ ነው (ገላትያ 5፥22)። ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ በፍሬዎቹ ሁሉ የሚሞላን የሰማነውን ስናምን ነው (ገላትያ 3፥5)። ስለዚህ፣ ጳውሎስ እየፀለየ ያለው እግዚአብሔር ከ”ክቡር ጕልበቱ” ጋር ያገናኘን ዘንድ ነው። መንገዱም የሚገናኘው በእምነት በኩል ነው።