እነርሱም “የእግዚአብሔር ልጅ ሆይ፤ ከእኛ ምን ጕዳይ አለህ? ጊዜው ሳይደርስ ልታሠቃየን መጣህን?” እያሉ ጮኹ። (ማቴዎስ 8፥29)
አጋንንቶች እዚህ ጋር አንድ ምስጢር ገብቷቸዋል፦ እንዳበቃላቸው ተረድተዋል። የእግዚአብሔር ልጅ እንደሚያሸንፍ የሚያውቁ ቢሆንም፣ ከመጨረሻው ሽንፈት በፊት ክርስቶስ እንደሚመጣባቸው ግን አያውቁም ነበር።
ክርስቶስ ወታደሮቹን ወደ ውግያ ለመምራት ጦርነቱ እስኪያልቅ አልጠበቀም። የዲያብሎስን መንግስት የሚያፈርስ ግብረ-ኅይል ወደ ሰይጣን ግዛት ይዞ ገብቷል። የመታደግ ሥራ የሚሠሩ ሕይወት ሰጪ ቡድኖች አሰልጥኖ አሰማርቷል። ከታላቁ እና ከመጨረሻው ድል በፊት፣ ትንንሽ ድሎችን አቅዷል።
ስለዚህ በጦርነት ጊዜ ሊኖረን የሚገባው አስተሳሰብ ይህ ነው፦ ሠይጣን እንድንከተለው በሚፈትነን ጊዜ መሸነፉ እርግጥ መሆኑን ራሱም ስለሚያውቀው እንስቅበታለን፤ “አብደሃል እንዴ? እንዴት ከተሸናፊ ጋር እቀላቀላለሁ?” እንለዋለን።
ቤተ ክርስቲያን ነፃ የወጣች “የዚህ ዓለም ገዢ” ጠላት ነች (2ኛ ቆሮንቶስ 4፥4)። እኛ አማኞች “በአየር ላይ ላሉት መንፈሳውያን ኀይላት ገዥ” የሆነውን የምንዋጋ ሽምቅ ተዋጊዎች ነን (ኤፌሶን 2፥2)።
በእርግጥ ውጊያው አደጋ የሞላበት እና ከሞት ጋር የምንጋፈጥበት ነው፣ ነገር ግን እጅግ አስደሳች ነው። በርግጥ ብዙ ነፍሳት ይጠፋሉ። ሰይጣን ከመቼውም ጊዜ ይልቅ ሰርጎ ገቦች ላይ ጨክኗል። ኢየሱስ ደግሞ በዚህ ዓለም ምቾትን እና ተቀባይነትን ቃል ባይገባልንም፣ እስከ ሞት ለሚጋደሉ ሁሉ ትንሣኤን እንደሚሰጥ አረጋግጧል።
ብዙዎች የአዛዣቸውን ትዕዛዝ በመፈጸም በደስታ ሕይወታቸውን ሰጥተዋል። ታዲያ ከዚህ የተሻለ ሕይወትም ሆነ ሞት የት ይገኛል?