እምነትን የሚሰብር መከራ | ሐምሌ 30

ነገር ግን ሥር የሌላቸው ስለሆኑ የሚቈዩት ለጥቂት ጊዜ ብቻ ነው፤ በቃሉ ምክንያት መከራ ወይም ስደት በመጣ ጊዜ ወዲያውኑ ይሰናከላሉ” (ማርቆስ 4፥17)።

የአንዳንዶች እምነት በመከራ ከመገንባት ይልቅ ፈርሷል። ኢየሱስ ይህንን አውቆ፣ እዚህ በአራቱ የመሬት ዐይነቶች ላይ በሰጠው ምሳሌ ላይ ገልጾታል። ቃሉን የሚሰሙ አንዳንድ ሰዎች በመጀመሪያ በደስታ ይቀበሉታል፤ ነገር ግን መከራ እንዲወድቁ ያደርጋቸዋል።

ስለዚህ መከራ ሁልጊዜ እምነትን ያጠነክራል ማለት አይደለም። አንዳንዴ እምነትን ያደቅቃል። ከዚያም “ላለው ይጨመርለታል፤ ከሌለው ላይ ግን፣ ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል” የሚለው የኢየሱስ ንግግር እውን ይሆናል (ማርቆስ 4፥25)።

ይህ፣ እምነታችን ከንቱ እንዳይሆንና ይበልጥ እንዲጠነክር (1ኛ ቆሮንቶስ 15፥2)፣ ወደፊት በሚገለጠው ጸጋ ባለ እምነት በመከራ እንድንጸና፣ ለእኛ የተደረገ ጥሪ ነው። “ላለው ይጨመርለታል” የሚለው እውነት በመከራ ውስጥ የእግዚአብሔርን ዕቅድ ማወቅ በመከራ አማካይነት ለማደግ ካሉ ዋና መንገዶች ውስጥ አንዱ ነው (ማርቆስ 4፥25)።

መከራችሁ ምንም ፋይዳ የሌለው፣ ወይም እግዚአብሔር የማይቆጣጠረው፣ አልያም ጭካኔ እንደሆነ የምታስቡ ከሆነ፣ መከራችሁ ከእግዚአብሔር ያርቃችኋል፤ ማድረግ እንደሚገባው ከሌሎች ነገሮች ሁሉ እናንተን ነጥቆ ወደ እግዚአብሔር ከማቅረብ ይልቅ የበለጠ ይለያችኋል። ስለዚህም በእግዚአብሔር ጸጋ ላይ ያለ እምነት፣ በመከራ አማካይነት ጸጋን የሚሰጥ መሆኑን ማመንን ያጠቃልላል።