እምነትን የሚያጠነክር መከራ | ሐምሌ 29

ወንድሞቼ ሆይ፤ ልዩ ልዩ መከራ ሲደርስባችሁ እንደ ሙሉ ደስታ ቍጠሩት፤ ምክንያቱም የእምነታችሁ መፈተን ትዕግሥትን እንደሚያስገኝ ታውቃላችሁ” (ያዕቆብ 1፥2-3)።

እንግዳ ቢመስልም እንኳ፣ በመከራ የምንናወጥበት ዋነኛው ዓላማ እምነታችንን የበለጠ ለማጽናት ነው።

እምነት ልክ እንደ ጡንቻ ነው፤ እስከ አቅሙ ጥግ ድረስ ብታስጨንቁት እንኳ፣ እየጠነከረ ይሄዳል እንጂ አይደክምም። በዚህ ክፍል ላይ ያዕቆብ እያለ ያለው ይህንን ነው። እምነትህ መሰባበር ደረጃ እስኪደርስ ድረስ አደጋ ላይ ሲወድቅ፣ ሲፈተን እና ጫና ሲደርስበት ውጤቱ ለመጽናት የሚያስችል የበለጠ አቅምና ጥንካሬ ይሆናል። ያዕቆብ ይህንን ጽናት ይለዋል።

እግዚአብሔር እምነት በጣም ደስ ስለሚያሰኘው ንጹሕና ጠንካራ እንዲሆን የመጨረሻ ልኩ ድረስ ይፈትነዋል። ለምሳሌ፣ በ2ኛ ቆሮንቶስ 1፥8-9 መሠረት በጳውሎስ ላይ ይህንኑ አድርጓል።

ወንድሞች ሆይ በእስያ ስለደረሰብን መከራ እንድታውቁ እንወዳለን፤ በሕይወት ለመኖር እንኳ ተስፋ እስከምንቆርጥ ድረስ ከዐቅማችን በላይ የሆነ ጽኑ መከራ ደርሶብን ነበር። በእርግጥም የሞት ፍርድ እንደተፈረደብን ይሰማን ነበር፤ ይህም የሆነው ሙታንን በሚያስነሣ በእግዚአብሔር እንድንታመን እንጂ፣ በራሳችን እንዳንታመን ነው።

“ይህም የሆነው” የሚሉት ቃላት፣ በዚህ ከባድ መከራ ውስጥ ዓላማ እንዳለ ያሳያሉ። ዓላማውም፣ ጳውሎስ በራሱ እና በሀብቱ ላይ ሳይሆን በእግዚአብሔር፣ በተለይም ሙታንን እንደሚያስነሣ በተገባው በእግዚአብሔር ተስፋ ጸጋ ላይ እንዲታመን ነው።

እግዚአብሔር እምነታችንን ሙሉ በሙሉ እርሱ ላይ መጣላችንን በጣም ስለሚፈልገው፣ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ፣ እንደ ጸጋው ብዛት በዚህ ዓለም ያለ ማንኛውም ልንመካበት የምንችለውን ነገር ሁሉ ሊወስድብን ይችላል፤ ሕይወትን እንኳ ቢሆን። ዓላማውም የሚያስፈልገን እርሱ ራሱ ብቻ እንደሆነ እንድናውቅና በእርሱ ላይ ያለን እምነት እንዲጨምር ነው።

ከመዝሙረኛው ጋር አብረን፣ “በሰማይ ከአንተ በቀር ማን አለኝ? በምድርም ከአንተ ሌላ የምሻው የለኝም። ሥጋዬና ልቤ ሊደክሙ ይችላሉ፤ እግዚአብሔር ግን የልቤ ብርታት፣ የዘላለም ዕድል ፈንታዬ ነው” እንድንል ይፈልጋል (መዝሙር 73፥25-26)።