“በዘላለም ኪዳን ደም የበጎች ታላቅ እረኛ የሆነውን ጌታችን ኢየሱስን ከሞት ያስነሣው የሰላም አምላክ፣ ፈቃዱን እንድታደርጉ በመልካም ነገር ሁሉ ያስታጥቃችሁ፤ ደስ የሚያሰኘውንም በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በእኛ ያድርግ፤ ለእርሱ እስከ ዘላለም ድረስ ክብር ይሁን፤ አሜን።” (ዕብራውያን 13፥20-21)
ክርስቶስ ያፈሰሰው የዘላለም ኪዳንን ደም ነው። በዚህ የተሳካ ቤዛነት፣ የራሱን የትንሣኤ በረከት አግኝቷል። “እግዚአብሔር … በዘላለም ኪዳን ደም … ጌታችን ኢየሱስን ከሞት ያስነሣው… ” ይለናል (ዕብራውያን 13፡20)። ይህ በዘላለም ኪዳን ደም ከሞት የተነሳው ኢየሱስ፣ አሁን ሕያው ጌታችን እና እረኛችን ነው።
ደግሞም በዚህ ሁሉ ምክንያት፣ እግዚአብሔር ሁለት ነገሮችን ያደርጋል፦
- ፈቃዱን እንድናደርግ በመልካም ነገር ሁሉ ያስታጥቀናል
- ደስ የሚያሰኘውን በእኛ ውስጥ ያደርጋል።
በክርስቶስ ደም የተገኘው “ዘላለማዊ ኪዳን” አዲሱ ኪዳን ነው። የአዲሱ ኪዳን ተስፋ ደግሞ ይህ ነው፦ “ሕጌን በልቡናቸው አኖራለሁ፤ በልባቸውም እጽፈዋለሁ” (ኤርምያስ 31፥33)። ስለዚህ፣ የዚህ ኪዳን ደም እግዚአብሔር ፈቃዱን እንድናደርግ እኛን ማስታጠቁን ብቻ ሳይሆን የሚያስረግጥልን፣ ማስታጠቁ ስኬታማ እንዲሆን በእኛ ውስጥ መሥራቱንም ጭምር ነው።
የእግዚአብሔር ፈቃድ በድንጋይ ወይም በወረቀት ላይ እንደ ጸጋ መገኛ ብቻ አልተጻፈም። በእኛ ውስጥ ተሠርቷል፣ ተጽፏል። ከዚህም የተነሳ፣ እግዚአብሔርን ይበልጥ ደስ በሚያሰኘው መንገድ ለማሰብ እና ለማድረግ እንነሳሳለን። ስሜቶቻችንንም እርሱን ወደሚያስደስተው ነገር ብቻ እንገራለን።
አሁንም ቢሆን የሰጠንን መሳሪያ እንድንጠቀም ታዘናል፦ “በፍርሀትና በመንቀጥቀጥ የራሳችሁን መዳን ፈጽሙ” ይለናል። ከዚያ በላይ ግን፤ ይህ ለምን እንደሚያስፈልግ ሲነግርን፦ “እንደ በጎ ፈቃዱ መፈለግንና ማድረግን በእናንተ ውስጥ የሚሠራ እግዚአብሔር ነውና” ይለናል (ፊልጵስዩስ 2፥12-13)።
እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት ከቻልን – በጎ ፈቃዱንም ከፈጸምን – ምክንያቱ ይህ ነው፦ በደም የተገዛው የእግዚአብሔር ጸጋ ከማስታጠቅ ሥራ አልፎ ሁሉን ቻይ በሆነው እውነተኛ መለውጥ ስለለወጠን ነው።