በሞት ጥላ ሸለቆ ውስጥ፤ ብሄድ እንኳ፣ አንተ ከእኔ ጋር ስለ ሆንህ፣ ክፉን አልፈራም፤ በትርህና ምርኵዝህ፣ እነርሱ ያጽናኑኛል። (መዝሙር 23፥4)
የመዝሙር 23 አቀማመጥ በራሱ ብዙ ነገር ያስተምረናል።
በመዝሙር 23፥1-3 ዳዊት እግዚአብሔርን “እርሱ” ብሎ በመጥራት እንዲህ ይናገራል፦
እግዚአብሔር እረኛዬ ነው። . . .
እርሱ ያሳርፈኛል . . .
እርሱ ይመራኛል። . . .
እርሱ ነፍሴን ይመልሳታል።
ከዚያም በመቀጠል በቁጥር 4 እና 5 ላይ፣ ዳዊት እግዚአብሔርን “አንተ” በማለት እንዲህ ያናግረዋል፦
አንተ ከእኔ ጋር ነህና ክፉን አልፈራም;
በትርህና ምርኵዝህ እነርሱ ያጽናኑኛል።
በፊቴ ማዕድ አዘጋጀህልኝ
ራሴን በዘይት ቀባህ።
ከዚያም በቁጥር 6 ላይ ደግሞ ተመልሶ፦
በእግዚአብሔር ቤት እኖራለሁ ይላል።
ከዚህ የምንማረው ትምህርት፣ ከእግዚአብሔር ጋር ሳናወራ ስለ እግዚአብሔር ብዙ ባናወራ መልካም መሆኑን ነው።
እያንዳንዱ ክርስቲያን፣ የሥነ መለኮት ምሑር ነው – ቢያንስ በጀማሪ ደረጃ። ማለትም የእግዚአብሔርን ባሕሪ እና መንገድ ለመረዳት፣ ደግሞም ያንን በቃላት ለመግለጽ የሚሞክር ነው። እንዲያማ ካልሆነ፣ ስለ እግዚአብሔር አንዳችን ለሌላችን የምንተናነጽበት አይኖርም። ከእራሱ ከእግዚአብሔርም ጋር አናወራም። ደግሞም አንዳችን የሌላችንን እምነት ለማጠንከር በእውነት የምናደርገው እርዳታ ጥቅም አይኖረውም።
ነገር ግን በመዝሙር 23 እና በሌሎች መዝሙሮች ላይ ከዳዊት የተማርኩት ነገር፣ ሥነ መለኮቴን ከጸሎት ጋር መቀላቀል እንዳለብኝ ነው። ስለ እግዚአብሔር የማወራውን ንግግር፣ እግዚአብሔርን በማናገር ደጋግሜ ማቋረጥ አለብኝ።
“እግዚአብሔር ቸር ነው”፣ የሚለውን ሥነ መለኮታዊ መግለጫ ከተናገርን በኋላ፣ “እግዚአብሔር ሆይ፣ ስለ ቸርነትህ አመሰግናለሁ!” የሚለውን ጸሎት ማስከተል አለብን።
“እግዚአብሔር ክቡር ነው” የሚለውን ንግግር፣ “ግርማህን አከብረዋለሁ” በማለት መደምደም አለብን።
የእግዚአብሔር እውነታ በልባችን እየተሰማን ከሆነ፣ እንዲሁም እያሰብነውና በከንፈሮቻችን እየገለጽነው ከሆነ፣ እንግዲያስ መሆን ያለበትን እያደረግን ነው።