እንባችሁን አነጋግሩት | ሚያዚያ 14

በእንባ የሚዘሩ፣ በእልልታ ያጭዳሉ። ዘር ቋጥረው፣ እያለቀሱ የተሰማሩ፣ ነዶአቸውን ተሸክመው፣ እልል እያሉ ይመለሳሉ። (መዝሙር 126፥5–6)

ዘር መዝራት ምንም የሚያስከፋ ነገር የለውም። የማጨድን ያህል እንኳ ስራ አይጠይቅም። ቀኖቹም ያማሩ ናቸው። ትልቅ የመኸር ተስፋም አብሮት አለ።

ሆኖም ግን ይህ መዝሙር፣ “በእንባ” ስለ መዝራት ይናገራል። አንድ ሰው “የሚዘራውን ዘር ተሸክሞ እያለቀሰ ወጣ” ይለናል። ለምን ይሆን የሚያለቅሰው?

ምክንያቱ፣ መዝራት የሚያስከፋ ወይም የሚከብድ ሆኖበት ነው ብዬ አላስብም። እንደማስበው ከሆነ፣ ማልቀሱ ከመዝራት ጋር ምንም ግንኙነት የለውም። መዝራት የሚወክለው በሕይወታችን ውስጥ የሚያስለቅሱን ነገሮች ሲኖሩ እንኳ፣ በቀላሉ መሥራት ያለብንን ሥራዎች ነው።

ሀዘናችንን እስክንጨርስ ወይም ችግሮቻችንን ሁሉ እስክንፈታ እህሉ ቆሞ አይጠብቀንም። በመጪው ክረምት መብላት ከፈለግን፣ አለቀስንም አላለቀስንም ወደ ማሳው ወጥተን መዝራት አለብን።   

የመዝሙሩ ተስፋ፣ ይህን ካደረጋችሁ “በእልልታ ታጭዳላችሁ” የሚል ነው። ነዶአችሁንን ተሸክማችሁ፣ እልል እያላችሁ ትመለሳላችሁ። ይህ የሚሆነው የመዝራት እንባ የማጨድ ደስታን ስለሚያስገኝ ሳይሆን፣ መዝራት በራሱ መኸሩን ስለሚያስገኝ ነው። ለቅሷችሁ መዝራትን እንድትተዉ በሚፈትናችሁ ጊዜ ይህን ማስታወስ ያስፈልጋችኋል።

ስለዚህ ይህን ለትምህርታችሁ ውሰዱ፦ ሊሰሩ የሚገባቸው ቀላልና ግልጽ ሥራዎች ኖረዋችሁ፣ ነገር ግን በሀዘን ተሞልታችሁ እንባ ሲተናነቃቸሁ፣ ተነሱና ሥራችሁን በእንባ ሥሩ። ተግባራዊ ሁኑ። እንባችሁን እንዲህ በሉት፦ “ይኸውልህ እንባዬ፣ ተረድቼሃለሁ። ተስፋ እንድቆርጥና ሁሉንም ነገር ዝርግፍ አድርጌ እንድተው ትፈልጋለህ። ነገር ግን የሚዘራ ማሳ አለብኝ (መታጠብ ያለበት ሰሃን፣ መጠገን ያለበት መኪና፣ መጻፍ ያለበት ስብከት አለብኝ)።” 

ከዚያም የእግዚአብሔርን ቃል መሠረት በማድረግ እንዲህ በሉት፦ “ይኸውልህ እንባዬ፤ መቼም ለዘላለም አትፈስስም። በእንባ ተሞልቼም እንኳ ቢሆን፣ ስራዬን ብቻ መስራቴ፣ በመጨረሻ የበረከት አዝመራን ያመጣልኛል። ስለዚህ፣ ከፈለክ መፍሰስህን ቀጥል። እስካሁን ባላየውም ወይም በሙላት ባይሰማኝም፣ እኔ ግን አምናለሁ። መዝራቴ ብቻ በቂ ነው፣ የመከር ነዶን ያመጣልኛል። እንባዬም ወደ ደስታ ይለወጣል።”