ረጃጅም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን ለመሸምደድ ዐሥር ምክንያቶች

የመጽሐፍ ቅዱስ ረጃጅም ክፍሎችን ብቻ ሳይሆን፣ ሙሉ አንድ መጽሐፍ ሳይቀር በቃላችሁ መያዝ ትችላላችሁ። ከባድ የጭንቅላት ጉዳት አሊያም ስትሮክ ወይም ሌላ ዓይነት ጉዳት ካለባቸው ጥቂት የማኅበረሰቡ ክፍል ካልተመደባችሁ በቀር ይህን ማድረግ ትችላላችሁ። ልታደርጉትም ደግሞ ይገባል። ይሁን እንጂ ይህን ማድረግ ያለባችሁ ለምንድን ነው?

  1.  የማስታወስ አቅማችሁ ዝቅተኛ ስለሆነ

የማስታወስ አቅሜ ዝቅተኛ ስለሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን መሸምደድ አልችልም አትበሉ። እንዲያውም መሸምደድ ያለባችሁ በዚህ ምክንያት ነው። እኔም የማስታወስ ብቃቴ ደካማ ነው። እውነቴን ነው ምላችሁ፤ የማስታወስ አቅሜ ከብዙ ሰዎች የወረደ እንደሆነ አስባለሁ። የማውቃቸውን እና በተደጋጋሚ የማገኛቸውን ሰዎች ስም እረሳለሁ። እጅግ ወሳኝ የሆኑ ነገሮችን ለረጅም ጊዜ እንዲቀመጥ የማደርገው ደካማውን አእምሮዬን አስጨንቄ ነው። ይህም የሚሆነው ነገሮችን በጊዜ ውስጥ በየዕለቱ በመደጋገም ሂደት (በመሸምደድ) ነው። ቀላል ስልት ቢኖራችሁ እና የተወሰነ ጥረት ብታደርጉ ልታሳኩት የምትችሉት ነገር ያስደንቃችሁ ነበር። አምስት የአዲስ ኪዳን መጽሐፍት የሸመደድኩ ሲሆን ስድስተኛዬን እየሸመደድኩ ነው። ይህም ደግሞ እኔ ደካማ የማስታወስ አቅም ስላለኝ ነው።

  1.  አእምሯችሁን መመገብ ስላለባችሁ

ፊልጵስዩስ 4፥8 እውነት የሆነውን ሁሉ፣ ክቡር የሆነውን ሁሉ፣ ትክክል የሆነውን ሁሉ፣ ንጹሕ የሆነውን ሁሉ፣ ተወዳጅ የሆነውን ሁሉ፣ መልካም የሆነውን ሁሉ እንድናስብ ይነግረናል። ይሁን እንጂ እንዲህ ያሉትን ነገሮች ካላስታወስናቸው ይህን እንዴት ልናደርግ እንችላለን? ድፍን አዎንታዊ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ፅንሰ ሐሳቦች ብዙም ጠቃሚ አይደሉም። ለብቻችን ሆነን ከተስፋ መቁረጥ ወይም ንዴት ወይም ምኞት ወይም ፍርሀት ጋር ትግል ስንገጥም፣ ከትውስታችን ልንመዛቸው የምንችላቸው ውስን ሁኔታ ላይ ያተኮሩ “የከበሩ ታላላቅ የተስፋ ቃሎች” ያስፈልጉናል (2ኛ ጴጥሮስ 1፥4)።

  1.  መጽሐፍ ቅዱስን በቀላሉ ልታገኙ ስለምትችሉ

አንድን ነገር በቀላሉ ማግኘት ስንችል ችላ ማለታችን ግር የሚል ነገር ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ሁልጊዜ በጠረጴዛችን ላይ፣ በስልካችን እና ኮምፒዩተራችን ላይ ካለ ከፍተን የተወሰኑ ክፍሎችን ልናነብብ፣ አንዳንዴም ቁልፍ ቃላትን በመጠቀም ሐሳቦችን ልንፈልግ እንችላለን። ይሁን እንጂ፣ ውስጣችን እንዲቀር ምንም ዓይነት ሸክም አይሰማንም። ይህንን ሽንገላ ልንዋጋው የምንችልበት አንደኛው መንገድ መጽሐፍ ቅዱስ በመሸምደድ ነው።

  1.  ኢንተርኔት ስላላችሁ

በሚያሳዝን ሁኔታ፣ እንዴት ማንበብ እንደሌለብን ኢንተርኔት እያስተማረን ነው። መረጃ አሳሾች እየሆንን ነው። በፍጥነት እናስሳለን፤ ግን ብዙም አናብላላም። ጥልቅ ለሆኑና በሚገባ ለተብራሩ ጽሑፎች ትዕግሥት እያጣን ነው። ረጃጅም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን መሸምደድ ትርጉሙ ምን እንደሆነ እና ከሕይወታችን ጋር እንዴት ልናዛምደው እንደምንችል እንድናስብ ያስገድደናል።

  1.  ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስን እንደሚገባ እናውቀዋለን ብላችሁ በምታስቡት ልክ ስለማታውቁት

ለረጅም ጊዜ ከምታውቋቸው ወዳጆቻችሁ ጋር እያወራችሁ ከዚህ በፊት የማታውቁት ገጽታ እንዳላቸው ልብ እንድትሉና ድንገት ደግሞ የበለጠ እንድትረዷቸው፣ እንዲሁም የበለጠ የቀረባችኋቸው እንደሆነ እንዲሰማችሁ ያደረገ ውይይት ገጥሟችሁ ያውቃል? ረጃጅም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን እና ሙሉ መጻሕፍትን ሳይቀር መሸምደድ የሚያደርግላችሁ ይህንን ነው። መልካም የመጽሐፍ ቅዱስ ወዳጆች ታማኝ የልብ ጓደኛ እና አማካሪ ሲሆኑ ታገኟቸዋላችሁ።

  1.  ምክንያቱም የእግዚአብሔር ቃል ይበልጥ የከበረ ስለሚሆንላችሁ

ያለንን ነገር የበለጠ የምናፈስበት ነገር ለእኛ የበለጠ የከበረ ይሆናል። መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ጥቂት ሰዓት የምታጠፉ ከሆነ ለእናንተ የከበረ እንዲሆን አትጠብቁ። ነገር ግን የክርስቶስ ቃል በውስጣችሁ በሙላት ይኖር ዘንድ ትልልቅ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን በልባችሁ ውስጥ በማጠራቀም ብዙ ሰዓቶችን የምታጠፉ ከሆነ የመሠረታዊ ሕይወታችሁ የከበረ አካል ይሆናል (መዝሙር 119፥11ቆላስይስ 3፥16ዘዳግም 32፤47)።

  1.  ምክንያቱም የእግዚአብሔርን ክብር የበለጠ ስለምታዩ

ከሚያደርጉት ነገር በመነሣት ስለ ሰዎች ልናውቅ የምንችለው ጥቂት ነገሮችን ብቻ ነው። በሚገባ ልናውቃቸው የምንችለው ከሚናገሩት ንግግር ነው። ተራሮች፣ ሕዋሳት፣ ጋላክሲዎች እና ፍየሎች እያንዳንዳቸው ስለ እግዚአብሔር የሚሉት ነገር አላቸው። ይሁን እንጂ እግዚአብሔርን የእውነት ለማወቅ፣ ስለ እግዚአብሔር የከበሩ ነገሮችን ለማየት እና ለመደመም እርሱ ራሱ ስለ ራሱ የሚለውን ነገር በጥንቃቄ ልናደምጥ ያስፈልጋል። ምክንያቱም እግዚአብሔር በዋነኝነት ራሱን የሚገልጠው በቃሉ ውስጥ ነው (1ኛ ሳሙኤል 3፥21)። ቃሉን መሸምደድ ድምጹን የበለጠ እንድንሰማ እና የበለጠ ክብር እንድንመለከት ያግዘናል።

  1.  ምክንያቱም ሽንገላን የመለየት አቅማችሁ እየጠራ ይመጣል

ዓለም ሁልጊዜ ትዋሻችኋለች። ዲያብሎስ የሐሰት አባት ነው (ዮሐንስ 8፥44)፤ ደግሞም ዓለም ሁሉ በእርሱ ኀይል ሥር ነች (1ኛ ዮሐንስ 5፥19)። ኀጢአታዊ ባሕርያችሁ ይዋሻችኋል። ሐሰተኛ ወንድሞችም ይዋሽዋችኋል። የእግዚአብሔርን ቃል የበለጠ ባወቃችሁ ቁጥር እንዲህ ያሉ ነገሮችን እንዴት ማስተናገድ እንዳለባችሁ በማወቅ የተካናችሁ ትሆናላችሁ (2ኛ ጢሞቴዎስ 2፥15)። ቃሉን በግልጽ በአእምሯችሁ ውስጥ በይበልጥ ስትይዙ የአጋንንትን ሽንገላ በመለየት ስኬታማ ትሆናላችሁ። ብዙ የእግዚአብሔር ቃል በአእምሯችሁ ውስጥ ሲኖር ሽንገላን የመለየት አቅማችሁ እየጠራ ይመጣል።

  1.  ምክንያቱም መከራ ስለሚገጥማችሁ

መከራ በመንገዳችሁ ነው (ወይም ደርሶባችኋል)። መከራ ግራ የሚያጋባ እና አቅጣጫ የሚያስት ነገር ነው። እንዲህ ላሉ ወቅቶች የሸመደድናቸው ረጃጅም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች በጣም ጠቃሚ ናቸው። ወደ አእምሯችሁ ከጉዳዩ ጋር የተያያዙ ጥቅሶች መምጣታቸው ብቻ ሳይሆን፣ በሕመም እና በፍርሀት ምክንያት ማስታወስ እንኳ ቢያቅታችሁ የት መሄድ እንዳለባችሁ ታውቃላችሁ። መጻሕፍትን መሸምደድ እነዚያን መጻሕፍት በአእምሯችሁ ላይ እንዲታተሙ ያደርጋል። ለመከራችሁ የሚናገሩ ምዕራፎች እና ክፍሎች የትኞቹ እንደሆኑ ታውቃላችሁ።

  1. ምክንያቱም ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ መከራ ስለሚገጥማቸው

ይህ ነገር በመከራ ውስጥ እያለፉ ላሉ ወንድሞች ወይም እህቶች የወንጌልን ማጽናናት እና ምክር ስናቀርብም ተመሳሳይ ነው። ረጃጅም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን መሸምደድ፣ እናንተን የሚጠቅም ብቻ ሳይሆን እምነትን የሚያጸና እውነት ክፉኛ ባስፈለጋቸው ጊዜ በማጋራት ሌሎችን የምንወድበት መንገድ ነው።

ረጃጅም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን የምንሸመድድበት መንገድ

መቃኘት፣ ማንበብ፣ በቃል ማለት፣ መደጋገገም

አንድ እና ሁለት ቁጥሮችን በመያዝ የምታደርጉት ሂደት ነው። እኔ እና ጆን ፓይፐር፣ እንዲሁም ሌሎች ብዙ ሰዎች አንድሩ ዴቪስ ያጎለበተውን በጣም ቀላል ስልት እንጠቀማለን። እንደ ምሳሌ ዮሐንስ 1፥1-3ን እንጠቀም።

[1] በመጀመሪያ ቃል ነበረ፤ ቃልም ከእግዚአብሔር ጋር ነበረ፤ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ።

[2] እርሱም በመጀመሪያ ከእግዚአብሔር ጋር ነበረ።

[3] ሁሉ ነገር በእርሱ ተፈጥሯል፤ ከተፈጠረው ሁሉ ያለ እርሱ የተፈጠረ ምንም የለም።

ቀን 1

  • ዮሐንስ 1፥1ን 10 ጊዜ ማንበብ (እያንዳንዱን ጊዜ ስታነብቡ ቃላቱን በአእምሯችሁ ላይ ለማተም አንብቡ)
  • ከዚያም መጽሐፍ ቅዱሳችሁን ዝጉት እና ዐሥር ጊዜ ደጋግሙት (ድምጻችሁን ከፍ አድርጋችሁ እንድትደጋግሙት አበረታታችኋለሁ)

ቀን 2

  • ዮሐንስ 1፥1ን ከልሱ ከዚያም በቃላችሁ አሥር ጊዜ ደጋግሙት
  • ዮሐንስ 1፥2ን ዐሥር ጊዜ አንብቡ
  • መጽሐፍ ቅዱሳችሁን ዝጉትና ዐሥር ጊዜ ደጋግሙት

ቀን 3

  • ዮሐንስ 1፥1ን አንድ ጊዜ በቃላችሁ በሉ
  • ዮሐንስ 1፥2ን ዐሥር ጊዜ በቃላችሁ ደጋግሙ
  • ዮሐንስ 1፥3ን ዐሥር ጊዜ አንብቡ
  • መጽሐፍ ቅዱሳችሁን ዝጉትና ዐሥር ጊዜ ደጋግሙት

እንዲህ እያለ ይቀጥላል። መከለስ፣ ማንበብ፣ በቃል ማንበብ፣ መደጋገገም። አንድን ቁጥር በቃላችሁ በቀን አንዴ ለመቶ ቀን ብትደጋግሙ ለረጅም ጊዜ እንድታስታውሱት ይቀመጣል።

ይህንን የመከለስ ልምድ ማዳበር እንዴት እንደምትችሉ ማወቅ ከፈለጋችሁ፣ አንድሩ ዴቪስ ይህንን እንዴት ማድረግ እንደምትችሉ የምታብራራ የ30 ገጽ መጽሐፍ አለችው።

ይህንን ማሳካት ትችላላችሁ። ልታደርጉትም ይገባል። ረጃጅም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን መሸምደድ እንደምታስቡት ከባድ አይደለም። ከላይ በተጠቀሱት ምክንያቶች እና ሌሎች ምክንያቶች የተነሣ በሕይወታችሁ ልታደርጉት የምትችሉት ወሳኙ ነገር ነው። መቼም ቢሆን አይጸጽታችሁም።