ሁሉን የሚያረካ አምላክ | መስከረም 25

በእግዚአብሔር ደስ ይበልህ፤ የልብህንም መሻት ይሰጥሃል። (መዝሙር 37፥4)

ደስታን መፈለግ አማራጭ አይደለም፤ በመዝሙር መጽሐፍ እንዲያውም ትዕዛዝ ነው፦ “በእግዚአብሔር ደስ ይበልህ፤ የልብህንም መሻት ይሰጥሃል” (መዝሙር 37፥4)።

መዝሙረኞቹም ማድረግ የፈለጉት ይህንን ነው፦ “ዋላ የምንጭ ውሃ እንደምትናፍቅ፣ አምላክ ሆይ፤ ነፍሴም እንዲሁ አንተን ትናፍቃለች። ነፍሴ አምላክን፣ ሕያው አምላክን ተጠማች፤ መቼ ደርሼ ነው የአምላክን ፊት የማየው?” (መዝሙር 42፥1-2)። “እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ አምላኬ ነህ፤ አንተን ከልብ እሻለሁ፤ ውሃ በሌለበት፣ በደረቅና በተራቈተ ምድር፣ ነፍሴ አንተን ተጠማች፤ ሥጋዬም አንተን ናፈቀች” (መዝሙር 63፥1)።

ተደጋግሞ ለተጠቀሰው ጥማት አቻ ስለሚሆነው እርካታ መዝሙረኛው እንዲህ ይላል፦ “ከቤትህ ሲሳይ ይመገባሉ፤ ከበረከትህም ወንዝ ይጠጣሉ” (መዝሙር 36፥8)።

የአምልኮ ሁሉ መሠረት ለሆነው ለእግዚአብሔር መልካምነት ክብር ምታቀርቡት፣ ግዴታዬ ነው ከሚል ፍርሀት የተነሣ መሆን የለበትም። በፍጹም! ደስ ልትሰኙበት የሚገባ ነገር ነው። “እግዚአብሔር ቸር መሆኑን ቀምሳችሁ እዩ፤ እርሱን መጠጊያ የሚያደርግ ምንኛ ቡሩክ ነው!” (መዝሙር 34፥8)። አዎ! ቅመሱት እና እዩት!

“ቃልህ ለምላሴ ምንኛ ጣፋጭ ነው! ለአፌም ከማር ወለላ ይልቅ ጣዕም አለው” (መዝሙር 119፥103)።

‘ሲ.ኤስ. ሉዊስ’ እንደሚለው፣ በመዝሙር መጽሐፍ ውስጥ እግዚአብሔር ሁሉን የሚያረካ አምላክ ነው። ፍጹም ደስታ የሚሰጣቸው ሕዝቦቹም ያለ መሸማቀቅ ይወዱታል (መዝሙር 43፥4)። እርሱ ሙሉ የሆነ እና የማይቋረጥ የእርካታ ምንጭ ነው፤ “የሕይወትን መንገድ ታሳየኛለህ፤ በአንተ ዘንድ የደስታ ሙላት፣ በቀኝህም የዘላለም ፍሥሓ አለ” (መዝሙር 16፥11)።