ለማስታወስ ትግል | ጥር 20

“ሆኖም ይህን አስባለሁ እንግዲያስ ተስፋ አለኝ፤ ያልጠፋነው ከእግዚአብሔር ታላቅ ፍቅር የተነሣ ነው፤ ርኅራኄው አያልቅምና።” (ሰቆቃወ 3፥21-22)

ከተስፋ ዋና ጠላቶች መሀል አንዱ የእግዚአብሔርን ኪዳኖች መርሳት ነው። ማስታወስ ደግሞ ታላቅ አገልግሎት ነው። ጴጥሮስና ጳውሎስ ለዚሁ ምክንያት ደብዳቤዎችን እንደጻፉ ተናግረዋል (2ኛ ጴጥሮስ 1፥13ሮሜ 15፥15)።

ማወቅ የሚያስፈልገንን እንድናስታውስ የሚረዳን ዋና አጋዣችን መንፈስ ቅዱስ ነው (ዮሐንስ 14፥26)። ይህ ማለት ግን ዝም ብለን መቀመጥ አለብን ማለት አይደለም። እኛም ራሳችን በማስታወስ የማገልገል ኅላፊነት አለብን። የመጀመሪያ የማስታወስ አገልግሎታችን የሚያስፈልገው ደግሞ እኛው ራሳችን ነን።

አእምሯችን አንድ ትልቅ ዓቅም አለው፦ አንድን ነገር በማስታወስ ከራስ ጋር ማውራት ይችላል። “ሆኖም ይህን ዐስባለሁ፤ እንግዲያስ ተስፋ አለኝ፤ ያልጠፋነው ከእግዚአብሔር ታላቅ ፍቅር የተነሣ ነው፤ ርኅራኄው አያልቅምና” (ሰቈቃወ 3፥21-22)።

እግዚአብሔር ስለ እራሱ ደግሞም ስለ እኛ የተናገረውን ካላስታወስን፣ በሐዘን እንኖራለን። ይህንንም ከልምድ አውቀዋለሁ። አእምሯችሁ ውስጥ ባሉ እግዚአብሔር የለሽ በሆኑ ሃሳቦች አትጠመዱ። እንደ እነዚህ ባሉት ማለት ነው፦ “… አልችልም” “… አታደርገውም” “… መቼም አይሆኑም” “… ሰርቶልኝ አያውቅም”።

እነዚህ ሀሳቦች ትክክል ሆኑም አልሆኑ ከእነርሱ የሚበልጠውን ካላስታወስን ወይም ካላሰብን፣ አእምሯችን እነዚህን እውነት የሚያደርግበትን መንገድ ሁሌም ያገኛል። እግዚአብሔር የማይቻለውን የሚችል አምላክ ነው። ከማይቻል ሁኔታ ውስጥ ሀሳባችንን ለማውጣት በከንቱ ከመታገል፣ እግዚአብሔር የማይቻልን ማድረግ እንደሚችል ማስታወስ ያዋጣል።

ስለ እግዚአብሔር ታላቅነት፣ ጸጋ፣ ኃይልና ጥበብ ደጋግመን ካላስታወስን፣ ጭፍንና ስሜት የለሽ ወደ መሆን ይወስደናል። “ስሜት የሌለውና አላዋቂ ሆንሁ፤ በፊትህም እንደ እንስሳ ሆንሁ” (መዝሙር 73፥22)።

በመዝሙር 77 ላይ፣ ከተስፋ መቁረጥ ወደ ተስፋ ሙሉነት ያለው ለውጥ በእነዚህ ቃላት ተገልጿል፦ “የእግዚአብሔርን ሥራ አስታውሳለሁ፤ የጥንት ታምራትህን በእርግጥ አስታውሳለሁ፤ ሥራህን ሁሉ አሰላስላለሁ፤ ድንቅ ሥራህን ሁሉ አውጠነጥናለሁ” (መዝሙር 77፥11-12)።

በህይወቴ ውስጥ ትልቁ ትግል ይሄ ነው። የእናንተም እንደሆነ አስባለሁ። ራሴን ከዚያም ሌሎችን ለማስታወስ መፋለም።