እግዚአብሔር እናንተን ከመጀመሪያ አንሥቶ በመንፈስ ተቀድሳችሁና በእውነትም አምናችሁ እንድትድኑ መርጧችኋል። (2ኛ ተሰሎንቄ 2፥13)
መፅሐፍ ቅዱስ፣ ዓለም ከመፈጠሩ አስቀድሞ፣ በጎም ሆነ ክፉ አንዳች ሳናደርግ፣ እግዚአብሔር በክርስቶስ እኛን ስለመምረጡ ይናገራል (ኤፌሶን 1፥4፣ ሮሜ 9፥11)። ስለዚህ፣ መመረጣችን ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ መሆኑ አጽናኦት ሊሰጠው ይገባል። ማመናችን ወይም መታዘዛችን በእግዚአብሔር ምርጫ ላይ ምንም ተፅዕኖ አያመጣም። ነፃ እና ፈጽሞ የማይገባን ነው።
በሌላ በኩል፣ በርካታ የመፅሐፍ ቅዱስ ክፍሎች፣ ከዘላለም በፊት መመረጣችንን የሚቃረን በሚመስል መልኩ — የመጨረሻውን ደህንነታችንን፣ በተለወጠ ልባችን እና ሕይወታችን ላይ የሚመሠረት አድርገው ያስቀምጡታል። ታዲያ ይህ የሚያስነሳው ጥያቄ፣ “የዘላለምን ሕይወት እንወርስ ዘንድ፣ በእምነት እና በቅድስና ለመቀጠላችን ምን ማረጋገጫ ማግኘት እንችላለን?” የሚል ነው።
መልሱ ደግሞ፣ ማረጋገጫችንን የምናገኘው በመመረጣችን ውስጥ ነው የሚል ነው። 2ኛ ጴጥሮስ 1፥10 እንዲህ ይላል፦ “ስለዚህ ወንድሞች ሆይ፤ መጠራታችሁንና መመረጣችሁን ለማጽናት ከፊት ይልቅ ትጉ፤ ምክንያቱም እነዚህን ብታደርጉ ከቶ አትሰናከሉም።” እግዚአብሔር እኔን ለማዳን ላለው ቁርጠኝነት መሠረቱ መለኮታዊ ምርጫ ነው። ስለዚህም፣ በጸጋው መርጦ ያስጀመረኝን መንገድ፣ በጸጋው እየቀደሰ ለፍጻሜ ያበቃዋል።
አዲሱ ኪዳን ይህ ነው። ኢየሱስ በሉቃስ 22፥20 ላይ “ይህ ጽዋ ስለ እናንተ በሚፈስሰው ደሜ የሚመሠረት አዲስ ኪዳን ነው” ብሏልና፣ በኢየሱስ የሚያምን ሁሉ በእርግጥ የአዲሱ ኪዳን ተካፋይ ነው። “የእኔ ለሆኑት ሁሉ በደሜ አዲሱን ኪዳን አረጋግጣለሁ” ብሎ ቃል ገብቶልናል።
በአዲሱ ኪዳን እግዚአብሔር ራሱ ታዛዥ ልብን ይሰጠናል እንጂ፣ እንዲያው በደፈናው ታዘዙ አይለንም። ታዛዥነትን ከመጠየቁ በፊት ይሰጠናል። “አምላክህን እግዚአብሔርን በፍጹም ልብህና በፍጹም ነፍስህ እንድትወድደው፣ በሕይወትም እንድትኖር፣ አምላክህ እግዚአብሔር የአንተንና የዘርህን ልብ ይገርዛል” (ዘዳግም 30፥6)። “መንፈሴን በውስጣችሁ አሳድራለሁ፤ ሥርዐቴን እንድትከተሉና ሕጌን በጥንቃቄ እንድትጠብቁ አደርጋለሁ” (ሕዝቅኤል 36፥27)። እነዚህ ሁሉ የአዲሱ ኪዳን ተስፋዎች ናቸው።
እግዚአብሔር ሕዝቡን ለማዳን ያለው ዘላለማዊ ቁርጠኝነት የተረጋገጠው በመለኮታዊ ምርጫ ነው። ስለዚህ፣ ምርጫ እግዚአብሔር በእምነት ያጸደቃቸውን በሙሉ እንደሚያከብራቸው ያረጋግጣል (ሮሜ 8፥30)። ይህ ማለት ለመክበር የተቀመጡትን መስፈርቶች ማሟላታችንን ለማረጋገጥ ያለመታከት በእኛ ውስጥ ይሠራል ማለት ነው።
በእርግጥም በእግዚአብሔር መመረጣችን ለመዳናችን ማረጋገጫ ነው። ለማዳን የቆረጠው እግዚአብሔር፣ ለመጨረሻው ድነት የሚያስፈልገንን ነገር ሁሉ ለመስጠትም የቆረጠ ነው።