የፍርድ ቀን መጽሐፍት | ሚያዚያ 6

ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ በታረደው በግ የሕይወት መጽሐፍ ላይ ስሞቻቸው ያልተጻፈ የምድር ሰዎች ሁሉ ለአውሬው ይሰግዳሉ። (ራእይ 13፥8)

በሕይወት መጽሐፍ ለተጻፉት ሁሉ ድነት የተረጋገጠ ነገር ነው።

በሕይወት መጽሐፍ መጻፍችን መዳናችንን የሚያረጋግጠው “የታረደው በግ የሕይወት መጽሐፍ” ተብሎ በመጠራቱ ነው። በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ያሉት ስሞች በጽድቅ ሥራቸው የዳኑ አይደሉም። የዳኑት በክርስቶስ መታረድ ነው።

ነገር ግን፣ ዮሐንስ በራዕይ 20፥12 ላይ፦ “ሙታንን፣ ታላላቆችንና ታናናሾችን በዙፋኑ ፊት ቆመው አየሁ፤ መጻሕፍትም ተከፈቱ። ሌላም መጽሐፍ፣ እርሱም የሕይወት መጽሐፍ ተከፈተ፤ ሙታንም በመጻሕፍቱ ተጽፎ በተገኘው መሠረት እንደ ሥራቸው መጠን ተፈረደባቸው” ይላል። ታድያ በክርስቶስ መታረድ ምክኒያት የዳንን ከሆነ፣ “በመጻሕፍት” ውስጥ የሚገኘው የሕይወታችን መዝገብ እንዴት ለፍርዳችን ይውላል?

መልሱ፦ ተግባራችንን የሚዘግቡት መጻሕፍቱ የክርስቶስ መሆናችንን በሚያሳዩ በቂ ማስረጃዎች ስለተሞሉ እምነታችንን እና ከክርስቶስ ጋር ያለንን አንድነት በአደባባይ ያረጋግጣሉ የሚል ነው።

ራእይ 21፥27ን ተመልከቱ፦ “በበጉ የሕይወት መጽሐፍ ከተጻፉት በስተቀር፣ ርኵሰትን የሚያደርግና ውሸትን የሚናገር ሁሉ አይገባባትም” ይላል፤ አዲሲቱን ኢየሩሳሌምን። እዚህ ጋር “በሕይወት መጽሐፍ” ውስጥ የመጻፍ ውጤቱ አለመጥፋት ብቻ ሳይሆን፣ አስጸያፊ እና ኃጢአተኛ ባሕሪያትንም አለመለማመድ ጭምር እንደሆነ ያሳየናል።  

ለምሳሌ፣ ከኢየሱስ አጠገብ የተሰቀለውን ሌባ አስቡ። ኢየሱስ በሉቃስ 23፥43 ላይ ይህ ሰው ወደ ገነት እንደሚገባ ተናግሯል። ታዲያ ግን መጻሕፍቱ ሲከፈቱ እርሱ ላይ የሚሆነው ፍርድ ምን ይመስል ይሆን? ከ99.9% በላይ የሚሆነው ሕይወቱ በኃጢአት የተሞላ ነበር።

ነገር ግን መዳኑ የሚረጋገጠው በክርስቶስ ደም ነው። ስሙ በታረደው በግ የሕይወት መጽሐፍ ውስጥ ይኖራል።

ከዚያም እግዚአብሔር መጽሐፎቹን ይከፍታል። በመጀመሪያም፣ የልጁን ከሁሉ የላቀ መሥዋዕትነት ለማክበር የዚህን ሰው የዕድሜ ልክ የኃጢአት ዘገባን ይጠቀማል። ከዚያም በመቀጠል፣ የመጽሐፉን የመጨረሻ ገጽ በመግለጥ በመስቀል ላይ የተከናወነውን የሌባውን አስደናቂ ለውጥ ያነባል። በመጻሕፍት ውስጥ ስለዚያ የመጨረሻው ቀን የተመዘገበው፣ ይህ በሕይወቱ የሆነው የእግዚአብሔር ሥራ፣ እምነቱን እና ከክርስቶስ ጋር ያለውን አንድነት በይፋ ያረጋግጣል። እናም የመዳኑ መሠረት ክርስቶስ እንጂ ሥራው አይሆንም።

ስለዚህ፣ በመጻሕፍት ተጽፎ ያለው፣ እምነታችንና ከክርስቶስ ጋር ያለንን አንድነትን በአደባባይ የሚያረጋግጥ ነገር ነው ስል፣ መዝገቡ ከመጥፎ ሥራ የበለጠ መልካም ሥራዎችን ይይዛል ማለቴ አይደለም።

እያልኩ ያለሁት፣ በመጻሕፍት ተጽፎ የሚገኘው የእምነትን፣ የዳግም ውልደት እና ከክርስቶስ ጋርም የመዋሃድ እውነታ የሚያሳይ በክርስቶስ ውስጥ ያለ ሕይወት ነው እያልኩ ነው። ክርስቲያን እንደመሆናችን እያንዳንዱን ቀን የምንኖረው ፍርዳችን ያለፈ እንደ ሆነ (ሮሜ 8፥1)፣ ስማችንም በሕይወት መጽሐፍ እንደተጻፈ እና በእኛም መልካምን ሥራ የጀመረው እርሱ እስከ ክርስቶስ ኢየሱስ ቀን ድረስ ከፍጻሜው እንደሚያደርሰው በመተማመን ነው።