ለሚሲዮናዊነት ሥራ የሚውለው የገና ሞዴል | ታሕሳስ 22

ወደ ዓለም እንደ ላክኸኝ እንዲሁ እኔ ወደ ዓለም ላክኋቸው።

የዮሐንስ ወንጌል 17፥18

ገና ለሚሲዮን (ወይም ለሚሽነሪነት) ሥራ የሚጠቅም ሞዴል ነው። ሚሲዮናዊነት የገና ነጸብራቅ ነው። “ልክ እንደ እኔ፣ እናንተም” የሚል ሐሳብ እናገኝበታለን።

አደጋዎቹን እንደ ምሳሌ ልንወስድ እንችላለን። ክርስቶስ ወደገዛ ወገኖቹ መጣ፤ የገዛ ወገኖቹ ግን አልተቀበሉትም። እናንተንም እንዲያው። በእርሱ ላይ ሴራ አሢረውበት ነበር፤ እናንተንም ላይ እንዲያው። እርሱ ዘላቂ ቤት አልነበረውም፤ እናንተም እንዲያው። የሐሰት ክስ ከምረውበት ነበር፤ እናንተም ላይ እንዲያው። ገርፈውት እና አፊዘውበት ነበር፤ እናንተም ላይ እንዲያው። ከሦስት ዓመት አገልግሎት በኋላ ሞተ። እናንተም እንዲያው።

ነገር ግን ከእነዚህ አደጋዎች ሁሉ የባሰውን አደጋ ክርስቶስ አምልጧል። እናንተም እንዲያው!

1506-1522 እ.ኤ.አ. በ16ተኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ፍራንሲስ ኤግዜቪየር የተባለ ሚሲዮናዊ አባ ፔሬዝ ለተባሉ የማላካ (የዛሬ ማሌዢያ አካባቢ) አባት ወደ ቻይና ባደረገው ሚሲዮናዊ ጉዞ ያጋጠመውን መከራ ሊገልጽላቸው እንዲህ ሲል ጻፈ፦ “ከአደጋዎቹ ሁሉ የከፋው አደጋ የሚከሰተው በእግዚአብሔር ምሕረት ላይ ያለን እምነት እና እርግጠኝነት የጠፋ ዕለት ነው… የእግዚአብሔር ጠላቶች ሁሉ ተሰብስበው ሊያደርሱብን ከሚችሉት ከየትኛውም አካላዊ ክፋት ሁሉ የሚብሰው በእርሱ ላይ ያለን እምነት መሸርሸር ነው፤ ያለ እግዚአብሔር ፈቃድ አጋንንትም ሆኑ የእነርሱ መጠቀሚያ ሰዎች አንድም እርምጃ ወደ ኋላ ሊይዙን አይችሉምና።”

አንድ ሚሲዮናዊ ሊያጋጥመው የሚችለው ከፍተኛው አደጋ ሞት ሳይሆን በእግዚአብሔር ምሕረት ላይ ሊያድርበት የሚችል ጥርጣሬ ነው። ያንን አደጋ ሊያመልጥ ከቻለ፣ ሊያጋጥሙት የሚችሉት ሌሎች አደጋዎች ሁሉ መውጊያ አይኖራቸውም። በመጨረሻም እግዚአብሔር ሁሉንም ጩቤ እና ስለት ለመንግሥቱ በትር ያደርገዋል። ጄ.ደብልዩ. አሌክሳንደር እንዲህ ብሏል፤ “አሁን ላይ ያለው እያንዳንዱ ድካም፣ በሚሊዮን ዓመታት ክብር በተትረፈረፈ መንገድ ይካሳል።” ክርስቶስ በእግዚአብሔር ካለመታመን አደጋ አምልጧል። በዚህ ምክንያት ደግሞ እግዚአብሔር ያለ ልክ ከፍ ከፍ አደረገው። እናንተንም እንዲሁ!

በዚህ የገና ሰሞን ስለ ክርስቶስ መወለድ ስታስቡ፣ ገና ለወንጌል ተልዕኮ እንደ ሞዴል ወይም እንደ ምሳሌ እንደሚያገለግል አስታውሱ። እኔ እንደሆንኩት፣ እናንተም እንዲሁ። ያ ተልዕኮ ደግሞ አደጋ ያለበት ነው። ከአደጋዎች ሁሉ ደግሞ የከፋው አደጋ የእግዚአብሔርን ምሕረት አለመታመን ነው። ለዚህ አደጋ እጃችሁን ከሰጣችሁ ሁሉም ነገር አከተመ ማለት ነው። እዚህ ጦርነት ላይ ካሸነፋችሁ ደግሞ፣ ለሚሊዮን ዓመታት የሚጎዳችሁ አንዳች አይኖርም።