ምክንያቱም ሁሉን ነገር እንዲታይ የሚያደርገው ብርሃን ነውና፤ ስለዚህም፣ “አንተ የተኛህ ንቃ፤ ከሙታን ተነሣ፤ ክርስቶስም ያበራልሃል” ተብሎአል። (ኤፌሶን 5፥14)
ኢየሱስ አልዓዛርን ከሞት እንዲነሣ ሲያዝዘው፣ አልዓዛር ትዕዛዙን የተከተለው እንዴት ነበር? ዮሐንስ 11፥43 እንዲህ ይላል፦ “በታላቅ ድምፅ፣ ̔አልዓዛር፣ ና ውጣ!’ ብሎ ተጣራ።” ይህ ትዕዛዝ ለሞተ ሰው የተሰጠ ትዕዛዝ ነበር። የሚቀጥለውም ቁጥር “የሞተውም ሰው እጅና እግሩ በቀጭን ስስ ጨርቅ እንደ ተጠቀለለ፣ ፊቱም በሻሽ እንደ ተጠመጠመ ወጣ” (ዮሐንስ 11፥44)። አልዓዛር ይህንን እንዴት ሊያደርግ ቻለ? የሞተ ሰው እንደገና ለመኖር የተሰጠውን ትዕዛዝ እንዴት ይታዘዛል? ብቸኛውም መልስ፣ ትዕዛዙ ራሱ አዲስ ህይወትን የመፍጠር ኃይል ስላለው ነው የሚል ነው። ትዕዛዙን መከተል ማለት በሕይወት ያሉ ሰዎች የሚያደርጉትን ማድረግ ማለት ነው። ይህ ደግሞ የሚሆነው ከትዕዛዝ ተቀባዩ ሳይሆን፣ ከአዛዡ ማንነት የተነሣ ነው።
ይህ በጣም አስፈላጊ ነው። “ከሞት ተነስ!” የሚለው የእግዚአብሔር ትዕዛዝ፣ ለመታዘዝ የሚያስችለንን ኃይል በውስጡ ይይዛል። የምንታዘዘው በራሳችን አቅም ሕይወትን በመፍጠር አይደለም። ይልቁንም፣ የምንታዘዘው በሕይወት ያሉ ሰዎች የሚያደርጉትን በማድረግ ነው – ልክ እንደ አልዓዛር። አልዓዛር ወጣ። ተነሣ። ወደ ኢየሱስም ተራመደ። የእግዚአብሔር ጥሪ ሕይወትን ይሰጣል። ይህ ጥሪ በሚሰጠው ኃይል እንታዘዛለን።
ጳውሎስ በኤፌሶን 5፥14፦ “አንተ የተኛህ ንቃ፤ ከሙታን ተነሣ፤ ክርስቶስም ያበራልሃል” ይላል። ከእንቅልፋችሁ እንድትነሱ የተሰጣችሁን ትዕዛዝ እንዴት ነው የምትከተሉት? ቤታችን መርዛማ በሆነ የከሰል ጭስ ቢሞላና የሆነ ሰው ሮጦ መጥቶ፣ “ተነስ፤ ራሳህን አድን!” ብሎ ጮሆ ቢቀሰቅሳችሁ፣ ራሳችሁን በመቀስቀስ ታዘዛችሁ ሊባል አይችልም። ታላቁ የጩኸት ድምጽ በራሱ ያነቃናልና። የምንታዘዘው ነቅተው ያሉ ሰዎች በአደጋ ጊዜ የሚያደርጉትን በማድረግ ነው። እንነሣና ከቤቱ እንወጣለን። ጥሪው ያነቃናል። ጥሪው በፈጠረው የንቃት ኃይል አማካኝነት እንታዘዛለን።
መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ዳግም ልደት የሚጋጩ የሚመስሉ ነገሮችን የሚናገረው ለዚህ ይመስለኛል። አዲስ ልብ ይኑራችሁ ይለናል፤ ነገር ግን ደግሞ አዲሱን ልብ መፍጠር የሚችለው እግዚአብሔር እንደሆነ ይነግረናል። ለምሳሌ፦
- ዘዳግም 10፥16 “የልባችሁን ሸለፈት ግረዙት”ይለንና፣ ዘዳግም 30፥6 “አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) የአንተንና የዘርህን ልብ ይገርዛል” ይለናል።
- ሕዝቅኤል 18፥31 “አዲስ ልብና አዲስ መንፈስ ይኑራችሁ”ይለንና፣ ሕዝቅኤል 36፥26 “አዲስ ልብ እሰጣችኋለሁ፤ አዲስ መንፈስም በውስጣችሁ አሳድራለሁ” ይለናል።
- ዮሐንስ 3፥7 “ዳግመኛ መወለድ አለባችሁ” ይለንና፣ 1ኛ ጴጥሮስ 1፥3 “እርሱ … እንደ ገና ወለደን” ይለናል።
የመወለድን ትዕዛዝ ለመታዘዝ፣ በመጀመሪያ መለኮታዊ የሆነውን የሕይወትንና የእስትንፋስ ስጦታ መቀበል አለብን፤ በመቀጠልም በህይወት ያሉ፣ የሚተነፍሱ ሰዎች የሚያደርጉትን ለማድረግ፦ በእምነት፣ በምስጋናና በፍቅር ወደ እግዚአብሔር መጮህ አለብን። የእግዚአብሔር ትዕዛዝ፣ በሚፈጥረውና በሚለውጠው የመንፈስ ቅዱስ ኃይል ሲመጣ፣ ሕይወትን ይሰጣል። እኛም እናምናለን፤ እንደሰታለን፣ እንታዘዛለን።