ስለዚህ ከሰማነው ነገር ስተን እንዳንወድቅ፣ ለሰማነው ነገር አብልጠን ልንጠነቀቅ ይገባናል። (ዕብራውያን 2፥1)
ሁላችንም ይህ ነገር የገጠማቸው ሰዎች እናውቃለን። ምንም ንቃት ወይም ጥንቃቄ አይታይባቸውም። ዐይናቸውን በኢየሱስ ላይ ለማተኮር እና እርሱን ለመስማት ችላ ይላሉ። ውጤቱም ባሉበት መቆም ሳይሆን መንሸራተት ነው።
ዝም ብሎ ባሉበት መቆም የሚባል ነገር የለም። የዚህች ዓለም ሕይወት ባለበት የሚቆም ሀይቅ ሳይሆን ወደጥፋት የሚፈስ ወንዝ ነው። ኢየሱስን ከልብ ካላዳመጣችሁት፣ ዕለት ተዕለት ካላስታወሳችሁት፣ ዐይናችሁንም እርሱ ላይ ካልተከላችሁ ባላችሁበት አትቆሙም፤ ወደኋላ ትመለሳላችሁ። ከክርስቶስ እየራቃችሁ ትሄዳላችሁ።
መንሸራተት በክርስትያን ህይወት ውስጥ አደገኛ ነገር ነው። በ ዕብራውያን 2፥1 መሠረት መፍትሔው ለሰማነው ነገር አብልጠን መጠንቀቅ ነው። ይህም ማለት እግዚአብሔር በልጁ በኩል የተናገረውን አተኩረን መስማት አለብን ማለት ነው። ዐይናችሁን እግዚአብሔር በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ በሚናገረው እና በሚያደርገው ነገር ላይ አተኩሩ።
ይህ ለማድረግ የሚከብድ ነገር አይደለም። ከኅጢአት ባህል እንዳንወጣ የሚከለክለን የኅጢአት ጉልበት ሳይሆን፣ በጥፋት ውስጥ አብሮ ለመሄድ ያለን ምኞት ነው።
እግዚአብሔር ከባድ ስራ ሰጥቶናል ብለን አናጉረምርም። እናዳምጥ፣ እናሰላስል፣ እናተኩር! ይህ ከባድ የሚባል ሥራ አይደለም። ሥራም አይደለም። ይልቁንም በኢየሱስ እንድንረካ እና በጥፋት እንዳንወሰድ የቀረበልን ግብዣ ነው።
ዛሬ እየተንሸራተታችሁ ከሆነ፣ ዳግም ለመወለዳችሁ እንደ ተስፋ የሚያግዛችሁ አንድ ነገር ቢኖር፣ ይህ መንሸራተታችሁ ይቆጠቁጣችኋል፤ ዕረፍትም አይሰጣችሁም። በውስጣችሁም በድጋሚ ለመቆም፣ ዐይናችሁን ወደ ኢየሱስ ለመመለስና እርሱን ሁልጊዜ ለማድመጥ ያለው ፍላጎት እያደገ ይመጣል።