ቀኑ ቀርቧል | ሚያዚያ 30

ሌሊቱ ሊያልፍ፣ ቀኑም ሊጀምር ነው። (ሮሜ 13፥12)

ይህ ቃል በመከራ እያለፉ ላሉ ክርስቲያኖች ተስፋን የሚሰጥ ነው። ኃጢአታቸውን ለሚጸየፉና ኃጢአት ከእነርሱ የሚወገድበትን ቀን ለሚናፍቁ ክርስቲያኖችም የተስፋ ቃል ነው። እንዲሁም የሁሉም ጠላት የሆነው ሞት፣ ድል ተደርጎ ወደ እሳት ባሕር የሚጣልበትን ቀን ለሚጠባበቁ ክርስቲያኖችም የተስፋ ቃል ነው (ራእይ 20፥14)።

ታዲያ ለእነዚህ ሁሉ እንዴት የተስፋ ቃል እንደሚሆን እንመልከት።

ከላይ የተጠቀሰው “ሌሊቱ” የሚለው ቃል፣ የዚህን የጨለማ ዘመን ኃጢአት፣ መከራና ሞትን ሁሉ የሚያመለክት ነው። እናም ጳውሎስ ስለዚህ ጉዳይ ምን ይላል? “ሌሊቱ ሊያልፍ … ነው።” የኃጢያት፣ የመከራ እና የሞት ዘመን ሊያልፍ ጊዜው ተቃርቧል። የጽድቅ፣ የሰላምና የደስታ ቀንም እየነጋ ነው።    

“ታዲያ ለመንጋት 2,000 ዓመታት አልረዘመም?” ልትሉ ትችላለችሁ። በአንድ በኩል ልክ ናችሁ። ስለዚህ፣ “አቤቱ እስከ መቼ፣ ኦ ጌታ ሆይ፣ እስከ መቼ እንዲህ እንዲቀጥል ትተወዋለህ?” ብለን እንጮኻለን። ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱሳዊ የሆነው አስተሳሰብ ይህ አይደለም። “እስከ መቼ!” ከሚለው ለቅሶ ያለፈ ነው። የዓለምን ታሪክ የሚመለከተው በተለየ መነጽር ነው።

ዋናው ልዩነቱ፣ “ቀኑ” የሚለው ቃል የሚያመለክተው፣ አዲሱን የመሲሑን ዘመን መሆኑ ነው። ያም ደግሞ በኢየሱስ ክርስቶስ ውስጥ በእርግጥ ነግቷል። ኢየሱስ የወደቀው የዚህ ዘመን ፍፃሜ ነው። ይኸውም፣ የዚህ የወደቀው ዘመን ፍጻሜ ወደ ምድር መጥቷል ማለት ነው። ኢየሱስ ሞትን ድል አድርጎ ሲነሳ፣ ኃጢአትን፣ ሕመምን፣ ሞትንና ሰይጣንን አብሮ ድል ነሥቶታል። የዘመኑ ወሳኙ ጦርነት አብቅቷል። መንግሥቱ መጥታለች። የዘላለምም ሕይወት መጥቷል።

በኢየሱስ መምጣት ምክኒያት ጎህ ሲቀድም — ማንም ሰው የቀኑን መምጣት መጠራጠር የለበትም። ንጋቱ 2,000 ዓመታትን ቢወስድም እንኳ። ጴጥሮስ በ2ኛ ጴጥሮስ 3፥8 ላይ እንዳለው፦ “ወዳጆች ሆይ፤ በጌታ ዘንድ አንድ ቀን እንደ ሺህ ዓመት፣ ሺህ ዓመትም እንደ አንድ ቀን መሆኑን ይህን አንድ ነገር አትርሱ።” ንጋት መጥቷል። ቀኑ ደርሷል። የንጋቷን ፀሐይ ሙሉ ለሙሉ ከመውጣት የሚያስቆማት ምንም ነገር የለም።