ባለጠጋ ለመሆን የሚፈልጉ ግን ወደ ፈተናና ወደ ወጥመድ፣ እንዲሁም ሰዎችን ወደ መፍረስና ወደ ጥፋት ወደሚያዘቅጠው ወደ ብዙ ከንቱና ክፉ ምኞት ይወድቃሉ። (1ኛ ጢሞቴዎስ 6፥9)
ስግብግብነት ነፍስን ለዘላለም የገሃነም ጥፋት ሊዳርጋት ይችላል።
ይህ ጥፋት፣ የመጨረሻው የገሃነም ሞት እንጂ ጊዜያዊ የሆነ የገንዘብ ኪሳራ እንዳልሆነ እርግጠኛ የምንሆንበት ምክንያት፣ ጳውሎስ ሶስት ቁጥሮችን ወረድ ብሎ በ1ኛ ጢሞቴዎስ 6፥12 ላይ በተናገረው ነገር ነው። ስግብግብነትን በእምነት መቃወም ይገባናል ይላል። ጨምሮም፣ “በብዙ ምስክሮች ፊት በመልካም መታመን የመሰከርህለትንና የተጠራህበትን የዘላለም ሕይወት አጥብቀህ ያዝ” በማለት ያስጠነቅቃል። ከስግብግብነት በመሸሽ እና እግዚአብሔር በሚሰጠን ጸጋ ለማመን እና ለመርካት በምናደርገው ውጊያ፣ ለማትረፍ የምንጥረው የዘላለም ሕይወታችንን ነው።
ስለዚህ፣ ጳውሎስ በ1ኛ ጢሞቴዎስ 6፥9 ላይ፣ ባለጠጋ የመሆን ፍላጎት ሰዎችን ወደ ጥፋት እንደሚከት ሲናገር፣ ስግብግብነት ትዳርን ወይም የንግድ ሥራን ሊያበላሽ ይችላል እያለ አይደለም (በእርግጥ ደግሞ ሊያበላሽ ይችላል!)። እያለ ያለው ግን ስግብግብነት ዘለዓለማችንን ሊያበላሽ ይችላል ነው። ወይም ደግሞ 1ኛ ጢሞቴዎስ 6፥10 መጨረሻ ላይ እንደሚለው ነው፦ “አንዳንዶች ባለጠጋ ለመሆን ካላቸው ጒጒት የተነሣ ከእምነት መንገድ ስተው ሄደዋል፤ ራሳቸውንም በብዙ ሥቃይ ወግተዋል።”
የስግብግብነት ወጥመድ ጣኦት አምልኮ እንደሆነ እና መጨረሻው ጥፋት ብቻ እንደሆነ እግዚአብሔር ምሕረት በተሞላው መንገድ ሊያስጠነቅቀን በቃሉ ብዙ ይለናል። መጨረሻው ሞት የሆነ አስከፊ፣ አታላይና ገዳይ ጎዳና ነው።
ስለዚህ፣ በ1 ጢሞቴዎስ 6፥11 ላይ የሚገኘው ቃል አጥብቀን እንያዝ፦ “ከዚህ ሁሉ ሽሽ።” በቴሌቪዥን፣ በበራሪ ወረቀት ማስታወቂያ፣ ኢንተርኔት ላይ ብቅ በሚሉ ምስሎች፣ ወይም ጎረቤቶቻችሁ በገዙት ነገር ሊሆን ይችላል። በየትኛውም መንገድ ወደ እናንተ ሲመጣ ስታዩት፣ ከአራዊት ሙዚየም ካመለጠ ከሚያገሳና ከተራበ አንበሳ እንደምትሮጡ አድርጋችሁ ሩጡ። “የዘላለምን ሕይወት አጥብቃችሁ ያዙ።”