የትናንት፣ የዛሬና የነገ ጸጋ | ነሐሴ 11

ይህን እያሰብን አምላካችን ለጥሪው የበቃችሁ አድርጎ እንዲቈጥራችሁ፣ መልካም ለማድረግ ያላችሁን ምኞትና ከእምነት የሆነውን ሥራችሁን ሁሉ በኀይሉ እንዲፈጽምላችሁ ዘወትር ስለ እናንተ እንጸልያለን። ደግሞም እንደ አምላካችንና እንደ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ መጠን የጌታችን የኢየሱስ ስም በእናንተ ዘንድ እንዲከብርና እናንተም በእርሱ እንድትከብሩ ይህን እንጸልያለን (2ኛ ተሰሎንቄ 1፥11-12)

ጸጋ ማለት በማይገባን ጊዜ እግዚአብሔር መልካም ማድረግ መፈለጉ ብቻ አይደለም። የእግዚአብሔር ጸጋ የማይገባንን ርሕራሔ ከመስጠት ባለፈ፣ ታላቅ የሆነ የእግዚአብሔር ኀይልም ነው። መልካም ነገር በእኛ እና ለእኛ እንዲሆን የሚያደርግ የማይገታ የእግዚአብሔር ኃይል ነው፤ ይህም ኀይል አሁንም ቢሆን የማይገባን ስጦታ ነው።

ጳውሎስ በቁጥር 11 ላይ ከእምነት የሆነውን ሥራችንን የምንፈጽመው “በኀይሉ” እንደሆነ ይነግረናል። በቁጥር 12 መጨረሻ ላይ ደግሞ “እንደ አምላካችንና እንደ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ መጠን” በማለት ጨምሮ ይናገራል። በሕይወታችን ውስጥ የሚሰራውና ክርስቶስን ከፍ የሚያደርገው የመታዘዝ ኀይል እውን የሆነው ከእግዚአብሔር ጸጋ የተነሳ ብቻ ነው።

በተጨማሪ ይህንን በ1ኛ ቆሮንቶስ 15፥10 ላይ ልታዩት ትችላላችሁ፦

“ነገር ግን በእግዚአብሔር ጸጋ አሁን የሆንሁትን ሆኛለሁ፤ ለእኔም የተሰጠኝ ጸጋ ከንቱ አልሆነም፤ እንዲያውም ከሁሉም በላይ በትጋት ሠርቻለሁ፤ ዳሩ ግን እኔ ሳልሆን ከእኔ ጋር ያለው የእግዚአብሔር ጸጋ ነው።”

ስለዚህ ጸጋው አሁን ላይ የሚሠራ፣ የሚለውጥ እና መታዘዝን የሚያስችል ኀይል ነው።

እንግዲያውስ፣ በኅይል ከእግዚአብሔር ወደ እናንተ በተወሰነ ጊዜ ውስጥ የሚንቀሳቀሰው ይህ ጸጋ፣ ባለፈ ጊዜ ውስጥ የነበረና ወደፊትም የሚኖር ነው። ባለፉት ጊዜያት ውስጥ በሕይወታችሁ ውስጥ የተሰራው ሥራ ባለፈ ጸጋ የተሰራ ሥራ ነው። ወደፊትም ደግሞ በእናንተ እና ለእናንተ ታላቅን ነገር ይሰራል፣ ስለዚህም የወደፊት ነው፤ በሚቀጥሉት አምስት ሰከንዶችም ሆነ አምስት ሚሊዮን ዓመታት፣ የእግዚአብሔር ጸጋ ወደፊት ይሰራል።

የእግዚአብሔር ጸጋ እንደማያልቅ ኀያል ወንዝ ነው። ከወደፊቱ የጸጋ ወንዝ ክምችት በሚያስፈልገን ጊዜ ወደዛሬ እየተንደረደረደ ይመጣልናል፣ ወዳለፈው የጸጋ ማጠራቀሚያ ውስጥም ይገባል። ለሚቀጥሉት አምስት ደቂቃዎች የሚያኖራችሁንና የሚደግፋችሁን ጸጋ ከወደፊቱ የጸጋ ወንዝ ትቀበላላችሁ፤ በዚያም ትታመናላችሁ። ደግሞም ባለፈው ጸጋ ማጠራቀሚያችሁ ውስጥ የአምስት ደቂቃ ዋጋ ያለው ጸጋን ታከማቻላችሁ፤ ለዚህም ጸጋ ጌታ አምላካችሁን ታመሰግናላችሁ።