ጲላጦስም፦ እንግዲያ ንጉሥ ነህን? አለው። ኢየሱስም መልሶ፦ እኔ ንጉሥ እንደ ሆንሁ አንተ ትላለህ። እኔ ለእውነት ልመሰክር ስለዚህ ተወልጃለሁ ስለዚህም ወደ ዓለም መጥቻለሁ፤ ከእውነት የሆነ ሁሉ ድምፄን ይሰማል አለው።
የዮሐንስ ወንጌል 18፥37
ዮሐንስ 18፥37 ለገና የሚሆን ግሩም ጥቅስ ነው፤ ምንም እንኳን በኢየሱስ ሕይወት ፍጻሜ አካባቢ የተነገረ ንግግር ቢሆንም።
እዚህ ጋር ከንግግሩ ልታስተውሉ የሚገባ ነገር ቢኖር፣ ኢየሱስ መወለዱን ብቻ ሳይሆን የተናገረው፣ ወደ ዓለም መምጣቱንም ጭምር ነው። የኢየሱስን ውልደት ልዩ የሚያደርገው ውልደቱ የሕይወቱ ጅማሮ አለመሆኑ ነው። በግርግም ከመወለዱ በፊት ሕልውና ነበረው። የናዝሬቱ ኢየሱስ ማንነት፣ ባሕርይ፣ እና ጠባይ ሁሉ ከመወለዱ በፊት የነበረ ነው።
ይህንን ሚስጥራዊ ሐሳብ የሚገልጸው ሥነ መለኮታዊ ቃል “ፍጥረት” የሚለው ሳይሆን፣ “ተሰግኦ” የሚለው ቃል ነው። የኢየሱስ መሠረታዊ ማንነት ሥጋ ለብሶ፣ ሰው ሆኖ ከመወለዱ በፊት የነበረ ነው። በመወለዱ አዲስ ሰው ሆኖ ካለመኖር ወደ መኖር መጣ እያልን ሳይሆን፣ በቁጥር የማይለካ ዕድሜ ያለው አካል ወደ ዓለም መጣ እያልን ነው። ከኢየሱስ ውልደት ከ700 ዓመታት በፊት ሚክያስ 5፥2 ላይ እንዲህ ተብሎ ተጽፎ ነበር።
“አንቺም ቤተ ልሔም ኤፍራታ ሆይ፥
አንቺ በይሁዳ አእላፋት መካከል ትሆኚ ዘንድ ታናሽ ነሽ፤
ከአንቺ ግን አወጣጡ ከቀድሞ ጀምሮ ከዘላለም የሆነ፥
በእስራኤልም ላይ ገዥ የሚሆን ይወጣልኛል።”
የኢየሱስን መወለድ ልዩ እና ምስጢራዊ የሚያደርገው ከድንግል መወለዱ ብቻ አልነበረም። እግዚአብሔር ከዚያ ተዓምር የሚበልጥ ሌላ ተዓምር ሊያከናውን አቅዶ ነበር። ይህም ተዓምር በገና ዕለት የሚወለደው ልጅ “ከቀድሞ ጀምሮ ከዘላለም የሆነ” መሆኑ ነው።
ስለዚህም ውልደቱ ዓላማ ነበረው። ከመወለዱ በፊት ስለመወለድ አስቦ ነበር። ከአባቱ ጋር በአብሮነት የታቀደ ዕቅድ ነበር። ያንን ታላቅ ዕቅድ ደግሞ በከፊል ሊሞት ሲል ተናግሮታል፦ “እኔ ለእውነት ልመሰክር ስለዚህ ተወልጃለሁ ስለዚህም ወደ ዓለም መጥቻለሁ፤ ከእውነት የሆነ ሁሉ ድምፄን ይሰማል አለው” (ዮሐንስ 18፥37)።
እርሱ ዘለዓለማዊው እውነት ነበር። የሚናገረው እውነት የሆነውን ብቻ ነበር። የፍቅርን ታላቁን እውነት በተግባር ፈጽሞታል። በተጨማሪም ከእውነት የተወለዱትን ሁሉ ወደ ዘለዓለማዊው ቤተሰቡ እየሰበሰበ ይገኛል። ከጥንት፣ ከዘለዓለም በፊት የነበረው ዕቅድ ይህ ነበር።