የወንጌል ግቡ | ነሐሴ 9

አሁን በደሙ ከጸደቅን፣ ይልቁንማ በእርሱ በኩል ከእግዚአብሔር ቊጣ እንዴት አንድንም! የእግዚአብሔር ጠላቶች ሳለን በልጁ ሞት ከእርሱ ጋር ከታረቅን፣ ዕርቅን ካገኘን በኋላ፣ በሕይወቱማ መዳናችን እንዴት የላቀ አይሆንም! ይህ ብቻ አይደለም። ነገር ግን አሁን ዕርቅን ባገኘንበት በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በእግዚአብሔር ደግሞ ሐሤት እናደርጋለን (ሮሜ 5፥9-11)።

መዳን የሚያስፈልገን ከምንድን ነው? ቁጥር 9 በግልጽ ያስቀምጠዋል፤ ከእግዚአብሔር ቁጣ። “አሁን በደሙ ከጸደቅን፣ ይልቁንማ በእርሱ በኩል ከእግዚአብሔር ቊጣ እንዴት አንድንም!” ታዲያ ግን፣ ከሁሉ የላቀውና የመጨረሻው የእርካታ ጥግ የሚገኝበት የወንጌሉ ሽልማት ይህ ነው በቃ?

አይደለም። ቁጥር 10 “በሕይወቱማ መዳናችን እንዴት የላቀ አይሆንም!” ይላል። ከዚያም ቁጥር 11 ደግሞ ከፍ ያደርገውና ወደ መጨረሻው የወንጌል ግብ እና ዓላማ ይወስደዋል፤ “ይህ ብቻ አይደለም። ነገር ግን አሁን ዕርቅን ባገኘንበት በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በእግዚአብሔር ደግሞ ሐሤት እናደርጋለን” ይላል።

ይህ የመጨረሻው እና ታላቁ የምሥራቹ ግብ ነው። ከዚህ በኋላ “ይልቁንም” የሚል ሌላ ቃል የለም። የሚልቅም ሌላ ነገር የለም። “ዕርቅን ባገኘንበት በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በእግዚአብሔር ደግሞ ሐሤት እናደርጋለን” በማለት እንዴት ወደዚያ እንደደረስን የሚገልጸውን የጳውሎስን ንግግር ብቻ ነው የምናገኘው።

ስለዚህ የወንጌሉ ግብ፣ “በእግዚአብሔር ሐሴት እናደርጋለን” የሚለው ነው። የወንጌል ከፍተኛው፣ ምሉዕ የሆነው እና እጅግ ጥልቅ የሆነው ጣፋጭ ግቡ እግዚአብሔር ራሱ ሲሆን፣ ከዚያም ደግሞ የተቤዥው ሕዝብ በእርሱ ደስ መሰኘቱ ነው።

በዚህም፣ በክርስቶስ የሚከፈለው ዋጋ (ሮሜ 5፥6-8) እና የሚገኘውም ሽልማት (ሮሜ 5፥11) ራሱ እግዚአብሔር ሆነ። አምላካችን ክፍያውም፣ ሽልማቱም ነው።

ወንጌል ማለት ለዘላለም በእግዚአብሔር ደስ መሰኘትን ራሱ እግዚአብሔር ለኛ የገዛበት የምሥራች ዜና ነው።