የእግዚአብሔርን ጸጋ አላቃልልም። (ገላትያ 2፥21)
ልጅ በነበርኩበት ወቅት፣ በአንድ ባህር ዳርቻ ስጫወት ድንገት እግሬ የረገጠበት መሬት ከዳኝና መርገጫ አጣሁ። በጣም ከመደንገጤ የተነሳ፣ በቅጽበት ወደ ውቅያኖሱ መካከል እየተጎተትኩ ያለው ያህል ተሰማኝ።
እጅግ በጣም አስፈሪ ገጠመኝ ነበር። አቅሜን ሁሉ ሰብስቤ በምን መንገድ ወደ ላይ እንደምወጣ ለማሰብ ሞከርኩ። ነገር ግን እግሬ መሬት መርገጥ አልቻለም። የባህሩም ሞገድ ኃይለኛ ስለነበር መዋኘት አልቻልኩም። ሲጀምርም ጥሩ ዋናተኛ አልነበርኩም።
በዚህ ድንጋጤዬ ውስጥ የማስበው ብቸኛ ነገር ሲረዳኝ የሚችል ሰው ይኖር ይሆን? የሚል ነው። ነገር ግን ከውኃው በታች ስለነበርኩ መጣራት እንኳን አልቻልኩም።
በዚህ ከባድ ጭንቀት ውስጥ እያለሁ፣ የአባቴ እጅ ክንዴን አጥብቆ ሲይዘኝ የተሰማኝን ስሜት ልገልጸው አልችልም። በዚህ ዓለም ላይ ካለ ከየትኛውም ስሜት ይልቅ ጣፋጭ ነበር። በእርሱ ጥንካሬ ለመሸነፍ ሙሉ በሙሉ ራሴን ሰጠሁ። በራሱ ፈቃድ ስላወጣኝ ተደሰትኩ። አልተቋቋምኩትም።
ነገሮች በጣም መጥፎ እንዳልሆኑ ለማስመሰል መሞከር እንዳለብኝ፣ ወይም በአባቴ ክንድ ላይ የእኔንም ጥንካሬ መጨመር እንደሚገባኝ፣ ሃሳቡ እንኳ ወደ አእምሮዬ አልመጣም። ያሰብኩት ይህንን ብቻ ነበር፦ አዎ! እፈልግሃለሁ! አመሰግንሃለሁ! ጥንካሬህን እወደዋለሁ! ተነሳሽነትህን እወደዋለሁ! አያያዝህን እወደዋለሁ! አንተ ታላቅ ነህ!
በዚህ በተሰጠ የፍቅር መንፈስ ውስጥ ማንም ሊመካ አይችልም። ይህንንም የተሰጠ ፍቅር “እምነት” ብዬ እጠራዋለው። ታዲያማ፣ በውኃው ውስጥ በጣም የፈለኩትና የተጠማሁት አባቴ፣ የእግዚአብሔር መጻዒ ጸጋ መገለጫ ነበር። ጸጋን የሚያጎላው እምነት ይህ ነው።
የክርስትናን ሕይወት እንዴት መኖር እንዳለብን ስናስብ፣ በዋነኝነት ልናተኩርበት የሚገባው፣ “የእግዚአብሔርን ጸጋ ከማቃለል ይልቅ እንዴት ማጉላት እችላለሁ?” የሚለው ላይ ነው። ጳውሎስ ይህንን ጥያቄ በገላትያ 2፥20-21 ይመልሳል፦ “ከክርስቶስ ጋር ተሰቅያለሁ፤ ከእንግዲህ እኔ አልኖርም፤ ነገር ግን ክርስቶስ በውስጤ ይኖራል። አሁንም በሥጋ የምኖረው ኑሮ በወደደኝና ስለ እኔ ራሱን አሳልፎ በሰጠው በእግዚአብሔር ልጅ ላይ ባለኝ እምነት ነው። የእግዚአብሔርን ጸጋ አላቃልልም።”
ለምንድን ነው የጳውሎስ ሕይወት የእግዚአብሔርን ጸጋ የማያቃልለው? ምክንያቱ፣ የሚኖረው በእግዚአብሔር ልጅ ላይ ባለው እምነት ስለሆነ ነው። እምነት ጸጋን ከማቃለል ይልቅ፣ ትኩረትን ሁሉ ወደ እርሱ በመሳብ ያጎላዋል።