ወደ እግዚአብሔር የሚያቀርበን ፍርሃት | ሰኔ 28

“አትፍሩ፤ ኀጢአት እንዳትሠሩ የእግዚአብሔር ፍርሃት ከእናንተ ጋር ይሆን ዘንድ፣ እግዚአብሔር ሊፈትናችሁ መጥቶአል።” (ዘፀአት 20፥20)

ባርያ የሚያደርገንና ከእግዚአብሔር የሚያርቀን የፍርሃት ዓይነት እንዳለ ሁሉ፣ ደግሞም ጣፋጭ የሆነና ወደ እግዚአብሔር የሚያቀርበን የፍርሃት ዓይነት አለ። ሙሴ በዘጸአት 20፥20 ላይ፣ ከአንዱ ፍርሃት እንድንጠበቅ ካስጠነቀቀን በኋላ ወደ ሌላኛው ፍርሃት ደግሞ ይጠራናል፦ “ሙሴም ለሕዝቡ፣ ‘አትፍሩ፤ ኀጢአት እንዳትሠሩ የእግዚአብሔር ፍርሃት ከእናንተ ጋር ይሆን ዘንድ፣ እግዚአብሔር ሊፈትናችሁ መጥቶአል’ አላቸው።”

እንደዚህ ላለው መልካም ፍርሃት ግልጽ የሆነ ምሳሌ አይቼ የማውቀው፣ ወንዱ ልጄ ጀርመን ሼፐርድ የሚባለውን ውሻ በዓይኖቹ ያየ ጊዜ ነው። በቤተ ክርስቲያናችን የሚገኙን አንድ ቤተሰብን እየጎበኘን ነበር። በወቅቱ ልጄ ካርስተን የሰባት ዓመት ልጅ ነበር። ታዲያ ይህ ውሻ ከግዝፈቱ የተነሳ ከሰባት ዓመቱ ልጄ ጋር አይን ለአይን ተፋጥጦ መቆም የሚችል ነው። 

ከዚያ ግን ይህ ውሻ ለማዳና ተግባቢ ነበር። ካርስተንም ቶሎ ለመግባባት የሚቸግረው ዓይነት ልጅ አልነበረም። ከዛ ግን የረሳነውን ዕቃ እንዲያመጣልን ካርስተንን ወደ መኪናው መልሰን ስንልከው፣ በሩጫ መሄድ ጀመረ፤ ውሻውም ዝግ ባለ አስፈሪ ማጉርምረም ከኋላው በሩጫ ተከተለው። እናም ይህ ካርስተንን በእርግጥ አስፈራው። የውሻው ባለቤት ግን፣ “ካርስተን ለምን ዝም ብለህ አትራመድም? ውሻው ሰዎች ከእርሱ ሸሽተው ሲሮጡ አይወድም” አለው።  

ካርስተን ውሻውን ቢያቅፈው፣ ለማዳና ተግባቢ ስለሆነ ፊቱን እንኳ እየላሰ ሊጫውተው ይችል ነበር። ነገር ግን ከውሻው ሸሽቶ ከሮጠ፣ ውሻው ያጉረመርምና ካርስተንን በፍርሃት ይሞላዋል።

ይህ እግዚአብሔርን መፍራት ምን ማለት እንደሆነ የሚያሳይ ምሳሌ ነው። እግዚአብሔር ኃይሉንና ቅድስናውን የሚያሳየን ፍርሃት በውስጣችን ይቀጣጠል ዘንድ ነው። ነገር ግን ከእርሱ ሊያባርረን ሳይሆን ወደ እርሱ ሊያቀርበን ነው። ከሁሉ በፊት፣ እግዚአብሔርን መፍራት ማለት እርሱ ታላቅ ዋስትናችን እና ብቸኛ እርካታችን ስለሆነ ከእርሱ መራቅን መፍራት ማለት ነው።

ወይም በሌላ አገላለጽ፣ መፍራት ያለብን አለማመንን ነው። በእግዚአብሔር ቸርነት ላይ አለመታመንን ፍሩ። የሮሜ 11፥20 ዋና አሳብ ይህ አይደለምን? “አንተም በእምነት ቆመሃል፤ ፍራ እንጂ ትዕቢተኛ አትሁን”። ይህ ማለት፣ ልንፈራ የሚገባን አለማመንን ወይም አለመታመንን ነው ማለት ነው። ከእግዚአብሔር መራቅን ፍሩ። ነገር ግን ኑሯችንን ሁሉ ከእርሱ ጋር ካደረግን፣ አብረነው ከተጓዝን እና አንገቱን ካቀፍነው፣ እርሱ የዘላለም ወዳጃችንና ጠባቂያችን ይሆናል።