እንግዲህ የምንናገረው ዋናው ነገር ይህ ነው፤ በሰማያት በግርማው ዙፋን ቀኝ የተቀመጠ እንዲህ ያለ ሊቀ ካህናት አለን፤ እርሱም በሰው ሳይሆን በጌታ በተተከለችው፣ እውነተኛ ድንኳን በሆነችው ቤተ መቅደስ አገልጋይ ነው … እነርሱ ያገለገሉት በሰማይ ላለችው መቅደስ ምሳሌና ጥላ በሆነችው ውስጥ ነው፤ ሙሴ ድንኳኒቱን ለመሥራት በተነሣ ጊዜ፣ “በተራራው ላይ በተገለጠልህ ምሳሌ መሠረት ሁሉን ነገር እንድታደርግ ተጠንቀቅ” የሚል ትእዛዝ የተሰጠው በዚህ ምክንያት ነበር።
ዕብራውያን 8፥1-2፣ 5 (አ.መ.ት)
ከዚህ በፊት አይተነው ነበረ፤ ተጨማሪ ደግሞ አለ። ገና ማለት ጥላውን በዋናው አካል መተካት ማለት ነው።
ዕብራውያን 8፥1-2፣ 5 የመደምደሚያ ዐይነት ዓረፍተ ነገር ነው። ዋነው ነጥብ በእኛ እና በእግዚአብሔር መካከል ገብቶ ከእግዚአብሔር ጋር የሚያስታርቀን እና የሚጸልይልን ሊቀ ካህናት በብሉይ ኪዳን ዘመን እንደነበሩት ደካማ፣ ኀጢአተኛ፣ ለሞት የተገዙ ሊቀ ካህናት አይደለም። የእግዚአብሔር ልጅ የሆነ፣ ብርቱ፣ ኀጢአት የሌለበት፣ እና ሊጠፋ የማይችል ሕይወት ያለው ነው።
ይህ ብቻ አይደለም። የሚያገለግለው ምድራዊ በሆነ፣ በቦታ እና በስፋት በታጠረ፣ በሚያረጅ እና ተባይ በሚያጠቃው፣ በሚበሰብስ እና በሚቃጠል፣ በሚቀደድ እና በሚሰረቅ የመገናኛ ድንኳን አይደለም። ክርስቶስ ስለ እኛ የሚያገለግለው በሰው ሳይሆን በጌታ በተተከለች እውነተኛ ድንኳን እንደሆነ ዕብራውያን 8፥2 ይነግረናል። ይህ ጥላው አይደለም። በመንግሥተ ሰማይ ያለው ዋነው ነገር ነው። በሲና ተራራ ላይ ሙሴ እንዲገለብጥ የተነገረው ጥላ የሚመነጨው ከዚህ ከዋናው አካል ነው።
ዕብራውያን 8፥1 በሚነግረን መሠረት ከጥላው የሚበልጠው እውነታ የሚነግረን ሌላ አስደናቂ ነገር፣ የኛ ሊቀ ካህናት በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ የተቀመጠ መሆኑ ነው። አንድም የብሉይ ኪዳን ሊቀ ካህናት ይህንን ከቶ ሊናገር አይችልም።
ኢየሱስ በቀጥታ ከእግዚአብሔር አብ ጋር ይነጋገራል። በእርሱ ዘንድ የከበረ ቦታ አለው። በእግዚአብሔር የተወደደ እና እጅግ የተከበረ ነው። ሁልጊዜ ከእግዚአብሔር ጋር ነው። ይህ እውነታ እንደ በፊቶቹ መጋረጃዎች፣ ሳህኖች፣ ጠረጴዛዎች፣ ሻማዎች፣ መጎናጸፊያዎች፣ ዘርፎች፣ በጎች፣ ፍየሎች፣ እና ርግቦች አይደለም። ይህ የመጨረሻው እና ጥላው ሲጠቁምለት የነበረው እውነታ ነው። እግዚአብሔር አብ እና ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ በፍቅር እና በፍጹም ቅድስና ሆነው ለእኛ የዘለዓለም ደኅንነት አብረው የሚሠሩት ታላቅ ሥራ!
ዋናውና የመጨረሻው እውነታ የሥላሴ አካላት በሕብረት ሆነው የእነርሱ የሆነውን ንግሥና፣ ቅድስና፣ ፍቅር፣ ፍትሕ፣ መልካምነት፣ እና እውነት በዳኑት ሕዝቦች እንዲታይ ማድረጋቸው ነው።