“ነገር ግን በምሕረቱ ባለጠጋ የሆነ እግዚአብሔር ለእኛ ካለው ከታላቅ ፍቅሩ የተነሣ፣ በበደላችን ሙታን ሆነን ሳለ፣ በክርስቶስ ሕያዋን አደረገን፤ የዳናችሁት በጸጋ ነው። እግዚአብሔርም ከክርስቶስ ጋር አስነሣን፤ በክርስቶስ ኢየሱስ በሰማያዊ ስፍራ ከእርሱ ጋር አስቀመጠን።” (ኤፌሶን 2፥4-6)
በመዳናችን ውስጥ የእግዚአብሔር ወሳኙ ስራ፣ “በበደላችን ሙታን ሆነን ሳለ፣ በክርስቶስ ሕያዋን” ማድረጉ ነው። በሌላ አነጋገር፣ በእርሱ ፊት ሙታን ነበርን። በድን፣ መንፈሳዊ ፍላጎት የሌለን፣ የክርስቶስን ውበት ልናይ የማንችል – በመንፈስ ዕውራን፣ ወሳኝ እና ዘለዓላማዊ ለሆኑ ነገሮች ሁሉ ሙታን ነበርን።
ነገር ግን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ – የክብሩ ዕቃ ለመሆን አንዳች ነገር ሳናደርግ – እግዚአብሔር ሥራውን ሠራ። ህያዋን አደረገን። በሉዓላዊነቱ ከመንፈሳዊ ሞት አነቃን፤ ይኽንንም ያደረገው የክርስቶስን ክብር እናይ ዘንድ ነው (2ኛ ቆሮንቶስ 4፥4)። ሞተው የነበሩት የመንፈስ ስሜቶቻችን በተዓምር ወደ ሕይወት መጡ።
ኤፌሶን 2፥4 ይህ “የምሕረት” ድርጊት ነው ይለናል። ማለትም እግዚአብሔር ሞታችንን ተመልክቶ አዘነልን። ወደ ዘላለም ሞትና ስቃይ የሚወስደውን የኅጢአትን ዋጋ ተመለከተ። “ነገር ግን በምሕረቱ ባለጠጋ የሆነ እግዚአብሔር… ሕያዋን አደረገን።” የምሕረቱ ባለጠግነት ባስፈለገን ጊዜ ተትረፈረፈልን። በዚህ ክፍል ውስጥ የሚገርመው ነገር ጳውሎስ የንግግሩን ፍሰት አቋርጦ፣ “የዳናችሁት በጸጋ ነው” ማለቱ ነው። “እግዚአብሔር … በክርስቶስ ሕያዋን አደረገን – የዳናችሁት በጸጋ ነው – ከክርስቶስ ጋር አስነሣን” ይለናል።
ጳውሎስ ይህንን በቁጥር 8 ይደግመዋል። የንግግሩን ፍሰት አቋርጦ ይህንን እዚህ ጋር ለምን ጨመረ? ትኩረቱ የእግዚአብሔር ምሕረት ለሞታችን ምላሽ መስጠቱ ላይ ሆኖ ሳለ፣ ጳውሎስ መዳናችን በጸጋ ጭምር መሆኑን ለምን መናገር ፈለገ?
ጳውሎስ ጸጋ ነፃ መሆኑን ለማጉላት ጥሩ ዕድል ነው ብሎ ስላሰበ ይመስለኛል። ከመለወጣችን በፊት ያለውን የሞተ ሁኔታችንን ሲገልፅ፣ የሞቱ ሰዎች ቅድመ ሁኔታዎችን ማሟላት እንደማይችሉ ተረድቷል። እንዲኖሩ ከተፈለገ፣ ፍጹም ቅድመ ሁኔታ የሌለውና ሙሉ በሙሉ ነፃ የሆነ የእግዚአብሔር የማዳን ስራ ያስፈልጋቸዋል። ይህ ነፃነት የጸጋ ዋና ሐሳብ ነው።
ሰውን ከሞት ከማስነሣት የበለጠ ከአንድ ወገን የሆነ ነፃ እና ያለ ድርድር የሆነ ምን ተግባር ይኖራል? በርግጥም የጸጋ ትርጉም ይህ ነው።