ፍጹም ነፃ የሆነው ፍቅር | ግንቦት 17

እነሆ፥ ሰማይ ሰማይ ሰማየ ሰማያትም፥ ምድርም በእርስዋም ያለው ሁሉ የአምላክህ የእግዚአብሔር ነው። ብቻ እግዚአብሔር ስለ አባቶችህ ደስ ብሎታል፥ እነርሱንም ወድዷል፤ ከእነርሱም በኋላ እናንተን ዘራቸውን እንደ ዛሬው ሁሉ ከአሕዛብ ሁሉ መካከል መረጠ። (ዘዳግም 10፥14-15)

እግዚአብሔር በምርጫው ያሳየው ፍቅር — ማለትም ሰዎችን ለራሱ የሚመርጥበት ፍቅር — ፍፁም ነፃ የሆነ ፍቅር ነው። ወሰን የለሽ ከሆነው ደስታውና ጥበቡ ያለማቋረጥ የሚፈስስ ነው።

ዘዳግም 10፥14-15፣ እግዚአብሔር እስራኤልን ከሌሎች የምድር ሕዝቦች ሁሉ በመምረጡ የተሰማውን ደስታ ያብራራል። እነዚህን ሁለት ነገሮች አስተውሉ፦

መጀመሪያ፣ በቁጥር 14 እና 15 መካከል ያለውን ልዩነት ተመልከቱ። ሙሴ፣ የእስራኤልን መመረጥ ዓለማት ሁሉ የእግዚአብሔር ከመሆናቸው ጋር አያይዞ ለምን ተናገረ? በቁጥር 14 ላይ፣ “ሰማያት፣ ሰማየ ሰማያት፣ ምድርና በእርሷም ያለው ሁሉ የአምላክህ የእግዚአብሔር ነው” ካለ በኋላ፣ በቁጥር 15 ላይ፣ “እናንተን ከአሕዛብ ሁሉ ለይቶ መረጣችሁ” ያለበት ምክንያት ምንድን ነው?

የዚህ ምክንያት እግዚአብሔር አማራጭ ስላልነበረው፣ ወይም በሆነ ምክንያት ስለተገደበ ብቻ እሥራኤልን እንዳልመረጠ ለማሳሰብ ይመስላል። “አንድ አምላክ የራሱ የሆነን አንድ ህዝብ ብቻ ይኖረዋል እንጂ፣ ሌላው ሁሉ የእርሱ ሊሆን አይችልም” የሚለውን በዘመኑ የነበረው ጣኦታዊ አስተሳሰብ ከንቱ አድርጎታል።

እውነቱ ይህ ነው፦ ያህዌ ብቸኛና እውነተኛ አምላክ ነው። አጥናፈ-ዓለሙ ሁሉ የእርሱ ነው። ስለዚህም፣ የፈለገውን ህዝብ ለራሱ መርጦ የመውሰድ መብትና ስልጣን አለው።

እናም ለእስራዔላውያን ሊነገር የማይችል አስገራሚ እውነት የሆነላቸው፣ እግዚአብሔር እነርሱን መምረጡ ነው። ግዴታ አልነበረበትም። የፈለገውን ሕዝብ መምረጥ ይችል ነበር። የማዳን ሥራውን ለመግለጥ ደስ ያሰኘውን ሕዝብ የመጥራት መብትም እድልም ነበረው። ካሻው ሁሉንም መምረጥ፣ ካልፈለገ ደግሞ ማንንም አለመምረጥ ሙሉ መብቱ ነበር።

ስለዚህ፣ እግዚአብሔር ራሱን “የእነርሱ አምላክ” ብሎ ሲጠራ፣ ከግብፅ ወይም ከከንዓን አማልክት ጋር ራሱን እኩል እያደረገ አይደለም። ሕዝቦቹም ሆነ አማልክቶቻቸው ሁሉ የእርሱ ናቸው። ቢፈልግ፣ ፈፅሞ የተለየ ህዝብን ለሥራው መምረጥ ይችል ነበር።

ቁጥር 14 እና 15ን እንደዚህ ባለው መልኩ ማስቀመጥ የተፈለገው፣ ፍፁም መብት እና ሉዓላዊ ሥልጣን ሁሉ የእግዚአብሔር ብቻ መሆኑን አጽናዖት ለመስጠት ነው።

ልናስተውለው የሚገባው ሁለተኛው ነገር፣ በቁጥር 15 ላይ፣ እግዚአብሔር ሉዓላዊ ነፃነቱን ተጠቅሞ አባቶቻቸውን መውደዱን ነው። “ብቻ እግዚአብሔር ስለ አባቶችህ ደስ ብሎታል፥ እነርሱንም ወድዷል“። የእስራኤልን አባቶች በመውደድ ደስ እንዲለው መረጠ።

እግዚአብሔር ለእስራኤል አባቶች የነበረው ፍቅር ፍፁም ነፃ እና በምህረት የተሞላ ነበር እንጂ፣ በእነርሱ አይሁዳዊ ባህርይ ወይም ብቃት ላይ የተመሰረተ አልነበረም።

ይህ በክርስቶስ ለምናምን ለእኛ ትምህርት ነው። እግዚአብሔር እንዲሁ በነፃ መርጦናል። አንዳች መልካም ነገር ስለተገኘብን ሳይሆን እንዲሁ ይህን ማድረግ ደስ ስላለው ብቻ በነፃ መርጦናል።