እግዚአብሔርን የማገልገል ትርፍ | ሰኔ 2

ይሁን እንጂ እኔን በማገልገልና የሌሎችን አገሮች ነገሥታት በማገልገል መካከል ያለውን ልዩነት ያውቁ ዘንድ፣ ለእርሱ ይገዛሉ። (2ኛ ዜና መዋዕል 12፥8)

እግዚአብሔርን ማገልገል ሌላ ማንንም ከማገልገል ፈጽሞ ይለያል።

እግዚአብሔር ይህንን እንድናውቅ እና በዚህም ደስ እንድንሰኝ እጥብቆ ይፈልጋል። ለምሳሌ፣ “እግዚአብሔርን በደስታ አገልግሉት” ብሎ አዝዞናል (መዝሙር 100፥2)። ለዚህ ደስታ ምክንያት አለው። በሐዋርያት ሥራ 17፥25 ላይ ተቀምጧል፦ “እርሱ ለሰዎች ሁሉ ሕይወትንና እስትንፋስን እንዲሁም ሌላውንም ነገር ሁሉ የሚሰጥ ስለሆነ፣ የሚጐድለው ነገር ባለመኖሩ በሰው እጅ አይገለገልም።”

እግዚአብሔርን በደስታ የምናገለግለው የእርሱን ጉድለት የማሟላት ቀንበር ስላልተጫነብን ነው። እርሱ ጎድሎበት ከእኛ የሚፈልገው ምንም ነገር የለም። ስለዚህ፣ እርሱን ማገልገል ማለት የሚያስፈልገውን ማሟላት ሊሆን አይችልም። ይልቁንም የሚያስፈልገንን ሁሉ ስለሚሞላብን በደስታ እናገለግለዋለን። እግዚአብሔር ማገልገል ማለት እርሱን ለማገልገል የሚያስፈልገንን ጸጋ ዘወትር ከእርሱ መቀበል ማለት ነው።

እግዚአብሔር ይህንን እንድናውቅ እና እንድንመካበት ምን ያህል አጥብቆ እንደሚፈልግ የሚያሳይ አንድ ታሪክ በ2ኛ ዜና መዋዕል 12 ላይ ተቀምጧል። የእስራኤል 10 ነገዶች ካመፁ በኋላ የደቡብን መንግስት ይገዛ የነበረው የሰለሞን ልጅ ሮብዓም፣ ጌታን ከማገልገል ይልቅ ሌሎች አማልክትንና መንግስታትን ሲመርጥ እናገኛለን።

እግዚአብሔርም በፍርዱ የግብፅ ንጉሥ ሺሻቅ፣ በ12,000 ሠረገላዎች እና በ60,000 ፈረሰኞች እንዲዘምትበት አደረገ (2ኛ ዜና መዋዕል 12፥2-3)።

እግዚአብሔር በምሕረቱ ነቢዩ ሸማያንን ወደ ሮብዓም እንዲህ ሲል ላከው፦ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘እናንተ ትታችሁኛል፤ ስለዚህ እኔም በሺሻቅ እጅ ትቼአችኋለሁ’” (2ኛ ዜና መዋዕል 12፥5)።  የዚህ መልዕክት አስደሳች ውጤት፣ ሮብዓም እና የእሥራኤል መሪዎች ራሳቸውን አዋርደው ንሰሀ በመግባት፣ “እግዚአብሔር ጻድቅ ነው” ማለታቸው ነበር (2ኛ ዜና መዋዕል 12፥6)።

ጌታም ራሳቸውን እንዳዋረዱ ባየ ጊዜ እንዲህ አላቸው፦ “ራሳቸውን ዝቅ አድርገው ስላዋረዱ እታደጋቸዋለሁ እንጂ አላጠፋቸውም፤ ቍጣዬም በሺሻቅ እጅ በኢየሩሳሌም ላይ አይፈስም” (2ኛ ዜና መዋዕል 12፥7)። ነገር ግን ለትምህርት በሚሆን ቅጣታቸው እንዲህ ይላቸዋል፦ “ይሁን እንጂ እኔን በማገልገልና የሌሎችን አገሮች ነገሥታት በማገልገል መካከል ያለውን ልዩነት ያውቁ ዘንድ፣ ለእርሱ ይገዛሉ” (2ኛ ዜና መዋዕል 12፥8)።

ዋናው ሐሳብ ግልጽ ነው፦ እግዚአብሔርን ማገልገል እና ጠላትን ማገልገል እጅግ የተለያዩ ናቸው። እንዴት? እግዚአብሔርን ማገልገል ከእርሱ በረከትንና ደስታን መቀበል ማለት ነው። ሺሻቅን ማገልገል ግን አድካሚ፣ ሙጥጥ የሚያደርግ እና በሐዘን የተሞላ ነው። እግዚአብሔር ሰጪ ነው። ሺሻቅ ግን ቀማኛ ነው።

ስለዚህም፣ በእሁድ ጠዋትም ሆነ በየዕለቱ እግዚአብሔርን ማምለክ አድካሚ የሥራ ሸክም ሳይሆን፣ ከእርሱ በደስታ የምንቀበልበት መንገድ መሆኑን በታላቅ ጉጉት እናውጃለን። እግዚአብሔር ከእኛ የሚፈልገው እውነተኛ አገልግሎት ያ ነው። “በምታደርጉት ነገር ሁሉ፣ እኔን እንደሰጪ እመኑኝ” ይለናል።