አባት ሆይ፤ እነዚህ የሰጠኸኝ፣ እኔ ባለሁበት እንዲሆኑ ዓለም ሳይፈጠር ስለ ወደድኸኝ የሰጠኸኝንም ክብሬን እንዲያዩ እፈልጋለሁ። (ዮሐንስ 17፥24)
በኢየሱስ የሚያምኑ በእግዚአብሔር ፊት እጅግ ውድ ናቸው። እኛም የክርስቶስ ሙሽራ ነን። ለኛ ካለው ታላቅ ፍቅር የተነሳ ይህ “ውድነታችን” ጣዖታችን እንዲሆን አይፈቅድም።
እግዚአብሔር በርግጥ ለእኛ ያለው ዋጋ እጅግ የከበረ ነው። ወደ ቤተሰቡ ማስገባቱ ይህንን ግልጽ ያደርግልናል። ነገር ግን ይህንን የሚያደርግበት መንገድ፣ ዓይኖቻችንን ከራሳችን ላይ አንስተን የእርሱን ታላቅነት እንድናደንቅ በማድረግ ነው።
እስቲ ራሳችሁን ፈትኑ። ኢየሱስ ቀኑን ከእናንተ ጋር ሊያሳልፍ መጥቶ ከጎናችሁ ተቀመጦ፣ “እጅግ በጣም እወድሃለሁ/እወድሻለሁ” ቢላችሁ፣ የቀረውን ቀን ከእርሱ ጋር ስታሳልፉ ምን ላይ ትኩረት ታደርጋላችሁ?
በርካታ መዝሙሮች እና ስብከቶች የሚተዉልን የተሳሳተ መልስ ይመስለኛል። የደስታችን ከፍታ ላይ የምንደረሰው እንደተወደድን ሲሰማን ነው የሚል አስተሳሰብ ይተዉልናል። “ይወደኛል!” “ይወደኛል!” አዎ፣ በእርግጥ ይህ ያስደስታል። ነገር ግን የደስታችን ጥግ ወይም ዋና ትኩረት እሱ አይደለም።
“ተወደድኩ” ስንል ምን እያልን ነው? ምን ማለታችን ነው? ይህ “መወደድ” ምንድን ነው?
ታላቁ እና ክርስቶስን የሚያከብረው ደስታ፣ ቀሪውን ጊዜ ሁሉ ዐይናችንን ዐይኖቹ ላይ በመትከል እና “ግሩም ነህ፣ ታላቅ ነህ” እያሉ በማወደስ ውስጥ የሚገኝ አይመስላችሁም ?
– ለከበደው ጥያቄ ሁሉ መልስ አለው፤ ጥበቡም እጅግ አስደናቂ ነው።
– አጸያፊውን እና የመገለውን ቁስል ይዳስሳል፤ ርኅራው እጅግ አስደናቂ ነው።
– የሞተችውን ሴት ከባለ መድኅኒቱ ፊት ለፊት ያስነሳል፤ ኅይሉ እጅግ አስደናቂ ነው።
– በዕለቱ የሚከሰቱትን ክስተቶች ይተነብያል፤ ሁሉን አዋቂነቱ እጅግ አስደናቂ ነው።
– የመሬት መንቀጥቀጥ እያለ እርሱ ግን ይተኛል፤ ድፍረቱ እጅግ አስደናቂ ነው።
– “አብርሃም ከመወለዱ በፊት እኔ፣ እኔ ነኝ” ይላል (ዮሐንስ 8፥58)፤ ቃላቱ እጅግ አስደናቂ ናቸው።
ከእርሱ ጋር የምናሳልፈውን ቀሪ ሰዓታት በሙሉ እያየነው ባለው ነገር ፈዘን እንቀራለን።
በቁጣው ከመንደድ ይልቅ፣ በእርሱ እንድንደነቅ እና ስለ እኛ መሞትን ጨምሮ ሊደረግልን የሚገባውን ሁሉ ማድረጉ ለእኛ ካለው ፍቅር የተነሳ አይደለም? መቤዠት፣ ማስተስረይ፣ ይቅርታ፣ ማጽደቅ፣ ማስታረቅ – እነዚህ ሁሉ መፈጸማቸው አስፈላጊ ነው። እነዚህ ሁሉ የፍቅር ድርጊቶች ናቸው።
ነገር ግን፤ እነዚህን ድርጊቶች የፍቅር ድርጊቶች የሚያደርጋቸው፣ የፍቅር ግቡ ነው። ግቡም፣ ወይም ዓላማውም፦ ከእርሱ ጋር በመሆን፣ አፍ የሚያስከፍት አስገራሚ ክብሩን እያየን መደነቅ ነው። እንዲህ ሲሆን፣ ራሳችንን ረስተን፣ እግዚአብሔር በክርስቶስ ውስጥ ለእኛ የሆነውን ሁሉ እየተመለከትን እናጣጥመዋለን፣ በግርማው እንደነቃለን፣ በክብሩም እንማረካለን።
ስለዚህ መጋቢያንን እና አስተማሪዎችን አሳስባለሁ፦ የሚሰሟችሁን ሰዎች በክርስቶስ የፍቅር ተግባራት በኩል አልፈው ወደ ፍቅሩ ግብ እንዲደርሱ ምሯቸው፣ አበረታቷቸው። የክርስቶስ ቤዛነት፣ የኀጢአት ስርየት፣ ይቅርታ፣ መጽደቅ፣ እርቅ እና የመሳሰሉት ግሩም እውነቶች፣ ኢየሱስን ወደማጣጣም እና በእርሱ ወደመደሰት ካልወሰዱን፣ ፍቅር አይደሉም።
ደጋግማችሁ አሳስቧቸው። ይህ ትኩረታችን ሊሆን ይገባል። ኢየሱስ በዮሐንስ 17፥24 የጸለየው ስለዚህ ጉዳይ ነው፦ “አባት ሆይ፤ እነዚህ የሰጠኸኝ፣ እኔ ባለሁበት እንዲሆኑ ዓለም ሳይፈጠር ስለ ወደድኸኝ የሰጠኸኝንም ክብሬን እንዲያዩ እፈልጋለሁ።”