ነገር ግን በመጨረሻው ዘመን የሚያስጨንቅ ጊዜ እንደሚመጣ ይህን ዕወቅ። ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ ይሆናሉ፤ ገንዘብን የሚወዱ፣ ትምክሕተኞች፣ ትዕቢተኞች፣ ተሳዳቢዎች፣ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፣ የማያመሰግኑ፣ ቅድስና የሌላቸው፣ … (2 ጢሞቴዎስ 3፥1–2)
አለማመስገን ከትምክህት፣ ከስድብ እና ከአለመታዘዝ ጋር እንዴት እንደተያያዘ አስተውሉ።
በሌላ ቦታ ደግሞ ጳውሎስ፦ “የሚያሳፍርና ተራ የሆነ ንግግር፣ ዋዛ ፈዛዛም ለእናንተ ስለማይገባ በመካከላችሁ አይኑር፤ ይልቁንስ የምታመሰግኑ ሁኑ” ይላል (ኤፌሶን 5፥4)። ስለዚህ ምስጋና እና አመስጋኝነት፣ የርኩሰት እና የሁከት ተቃራኒ ሆኖ ተቀምጧል።
ይህ የሆነበት ምክንያት፣ የምስጋና ስሜት የትሕትና እንጂ የኩራት ስሜት ስላልሆነ ነው። አመስጋኝ ሰው ከራሱ ይልቅ ሌሎችን ከፍ ከፍ የሚያደርግ ነው። ደስተኛ ልብ እንጂ ቁጡ ወይም መራራ አይደለም። በመራርነት ውስጥ ያለ ምስጋና እርስ በእርሱ ይጋጫል።
ምሬትን፣ ንቀትንና ዓመፅን በማሸነፍ የአመስጋኝ ልብን ለመጎናጸፍ ቁልፉ፥ ፈጣሪ፣ ደጋፊ፣ ረድኤት እና ተስፋ ሰጪ በሆነው እግዚአብሔር ላይ ጠንካራ እምነትን ማኖር ነው። ባለን እና ሊኖረን ተስፋ ባረግነው ነገር ሁሉ፣ ለእግዚአብሔር ጥልቅ ውለታ እንዳለብን ከካድን፣ የምስጋናችን ምንጭ ደርቋል ማለት ነው።
ስለዚህ፥ በዚህ በመጨረሻው ዘመን፣ የግፍና የዘለፋ፣ እንዲሁም የርኩሰት እና የአለመታዘዝ መበራከት ምክንያቱ ከእግዚአብሔር ጋር ያለን ግንኙነት መበላሸቱ ነው። የችግሩም ዋና መሠረት፣ ፍጹም ጥገኞች ሆነን ሳለ ምስጋናን መንፈጋችን ነው።
ለእግዚአብሔር የሚሰጠው የላቀው የምስጋና ምንጭ በተራራው አናት ላይ ሲደርቅ፣ ብዙም ሳይቆይ፣ ከተራራው ግርጌ ያሉት ሁሉም የምስጋና ጅረቶች ከተራራው የበለጠ መድረቅ ይጀምራሉ። ምስጋና ሲጠፋ፣ የእኔነት ስሜት ለተድላው ሲል ውድቀትን ከመቀበል ወደኃላ አይልም።
በትሕትና የተሞላ ታላቅ ምስጋና እንዲኖራችሁ አጥብቃችሁ ጸልዩ።