በድካማችን የማይራራልን ሊቀ ካህናት የለንምና፤ ነገር ግን እንደ እኛ በማንኛውም ነገር የተፈተነ ሊቀ ካህናት አለን፤ ይሁን እንጂ ምንም ኀጢአት አልሠራም። (ዕብራውያን 4፥15)
“በሕይወቴ ውስጥ ጥልቅ ትምህርቶችን የተማርኩት በዕረፍትና በምቾት ጊዜያቶቼ ውስጥ ነው” ሲል ማንንም ሰምቼ አላውቅም። ከዚህ ይልቅ፣ በርካታ ብርቱ ቅዱሳን እንዲህ ሲሉ ሰምቻለሁ፦ “የእግዚአብሔርን ጥልቅ ፍቅር የተረዳሁትና ከእርሱም ጋር ጥልቅ ወደ ሆነ ግንኙነት የገባሁት በከባድ መከራ ውስጥ ባለፍኩበት ወቅት ነበር” ይላሉ።
ይህ የሚያሰክን መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነት ነው። ለምሳሌ ፊልጵስዩስ 3፥8 እንዲህ ይላል፦ “ለእርሱ[ለክርስቶስ] ስል ሁሉን ዐጥቻለሁ፤ ክርስቶስን አገኝ ዘንድ ሁሉን እንደ ጒድፍ እቈጥራለው።” በሌላ አገላለጽ፦ ሕመም ከሌለ፣ ትርፍ የለም ማለት ነው። ወይም ደግሞ፦ ክርስቶስን አብዝቶ የሚሰጠኝ ከሆነ፣ ሁሉንም ነገሬን ዛሬውኑ መስዋዕት አደርጋለሁ እንደ ማለት ነው።
በተጨማሪም፣ ዕብራውያን 5፥8፣ “የእግዚአብሔር ልጅ ቢሆንም እንኳ፣ [ኢየሱስ] ከተቀበለው መከራ መታዘዝን ተማረ” ይለናል። ያው እራሱ መልዕክትም ምንም ኀጢአት እንዳልሰራ ይገልጽልናል (ዕብራውያን 4፥15)።
ስለዚህ መታዘዝን መማር ማለት ከአለመታዘዝ ወደ ታዛዥነት መቀየር ማለት አይደለም። በመታዘዝ ልምምድ ውስጥ ከእግዚአብሔር ጋር በጥልቀት እያደጉ መሄድ ማለት ነው። ይህ ማለት ጥልቅ የሆነ ለእግዚአብሔር መሰጠትን መለማመድ ማለት ነው። ይህ ውጤት ደግሞ የሚገኘው በመከራ ውስጥ ሲታለፍ ብቻ ነው። ሕመም ከሌለ፣ ትርፍ የለም።
በ17ተኛው ክፍለ ዘመን ይኖር የነበረው ሳሙኤል ራዘርፎርድ በመከራ ጉድጓድ ውስጥ በተጣለ ጊዜ፣ ታላቁ ንጉሥ ሁልጊዜም ወይኑን በዚያ እንደሚያስቀምጥ እንዳስታወሰ ተናግሯል። እውቁ ሰባኪ ቻርልስ ስፐርጅንም፦ “በመከራ ባህር ውስጥ ወደ ጥልቁ የሚገቡ፣ ብርቅዬ ዕንቁዎችን ያወጣሉ” ብሏል።
ካንሰር እንደያዛችሁ እንድትጠረጥሩ የሚያደርግ እንግዳ ህመም ሲሰማችሁ ወዳጆቻችሁን የበለጠ እንድትወዷቸው አያደርጋችሁም? በእርግጥም ግራ የምንገባ ፍጥረት ነን። ጤና እና ሰላም ኖሮን ሌሎችን ለመውደድ ጊዜ እንዳለን ካሰብን፣ ፍቅራችን ስስና የችኮላ ይሆናል። ሞታችን የቀረበ እንደሆነ ስናስብ ግን፣ ፍቅራችንም ጥልቀት ያለው፣ እርግት ያለ፣ ሊገለጽ የማይችል የደስታ ወንዝ ይሆናል፤ እናም ይህን ፍቅር ላለማጣት እንተጋለን።
ስለዚህ ወንድሞችና እህቶቼ፣ “ልዩ ልዩ መከራ ሲደርስባችሁ እንደ ሙሉ ደስታ ቍጠሩት” (ያዕቆብ 1፥2)።