በበደላችን ሙታን ሆነን ሳለ፣ በክርስቶስ ሕያዋን አደረገን፤ የዳናችሁት በጸጋ ነው። (ኤፌሶን 2፥5)
የሚስዮናውያን ታላቁ ተስፋ ወንጌል በመንፈስ ቅዱስ ኅይል ሲሰበክ፣ ሰው ሊፈጥረው የማይችለውን የሚያድነውን እምነት እግዚአብሔር ራሱ ይፈጥራል የሚለው ተስፋ ነው። የእግዚአብሔር ጥሪ የሰው ጥረት ማድረግ ያልቻለውን ይፈፅማል። የሞቱትን ያስነሳል፤ መንፈሳዊ ሕይወትን ይፈጥራል። ኢየሱስ አልአዛርን ከመቃብሩ እና ውጣ ብሎ ሲጠራው፣ ይህም ጥሪ ሕይወትን በመሰጠት መታዘዝን እንደፈጠረ፣ ማንም ሰው የሚድነውም ልክ እንደዚህ ነው (ዮሐንስ 11፥43)።
እኛ በጥሪያችን ሌሎችን ከእንቅልፋቸው ማስነሣት እንችል ይሆናል፤ የእግዚአብሔር ጥሪ ግን የሌሉ ነገሮችን ሁሉ በመጥራት ካለመኖር ወደ መኖር ያመጣቸዋል (ሮሜ 4፥17)። የእግዚአብሔርን ጥሪ መቋቋም ወይም እምቢ ማለት አይቻልም። እግዚአብሔር ያቀደውን ከማሳካት ጎድሎ አያውቅም። ጳውሎስ ይህን ለማሳየት እንዲህ ብሏል፦ “አስቀድሞ የወሰናቸውን ጠራቸው፤ የጠራቸውን አጸደቃቸው” (ሮሜ 8፥30)።
በሌላ አነጋገር፣ የእግዚአብሔር ጥሪ ያለመውን ከማሳካቱ የተነሣ፣ አንድ ሰው ሊጸድቅበት የሚችልበትን እምነት የመፍጠር ኅይል አለው። እንደ ሮሜ 8፥30 ከሆነ የተጠሩት ሁሉ ጸድቀዋል፤ ያለ እምነት ግን የፀደቀ የለም (ሮሜ 5፥1)። ስለዚህ የእግዚአብሔር ጥሪ የፈለጋቸውን ሁሉ ያለ ተቃውሞ ወደ ሚያጸድቀው እምነት ያመጣቸዋል ማለት ነው።
ሰው ግን ይህንን ማድረግ በፍፁም አይቻለውም። የድንጋዩን ልብ መቀየር የሚችለው እግዚአብሔር ብቻ ነው (ሕዝቅኤል 36፥26)። ሰዎችን ወደ ልጁ መሳብ የሚችለው እግዚአብሔር ብቻ ነው (ዮሐንስ 6፥44፣ 65)፤ በመንፈስ የሞተውን ልብ ለወንጌል ጆሮ እንዲሰጥ ማድረግ የሚችለው እግዚአብሔር ብቻ ነው (ሐዋርያት 16፥14)። በጎቹን በስማቸው የሚያውቃቸው፣ እንዲከተሉት ልባቸውን በሚስብ መልኩ የሚጠራቸው፣ አንዳይጠፉም የሚጠብቃቸው መልካሙ እረኛ ኢየሱስ ብቻ ነው (ዮሐንስ 10፥3-4፣ 14)።
የእግዚአብሔር ሉዓላዊ ጸጋ ለሰው የማይቻለውን ነገር በኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል መፈጸሙ የሚስዮናውያን ታላቁ ተስፋ ነው።