ልጆች ሆይ፤ ኀጢአታችሁ ስለ ስሙ ተሰርዮላችኋልና፣ እጽፍላችኋለሁ። (1ኛ ዮሐንስ 2፥12)
እግዚአብሔር ሰዎችን የሚወድደው፣ ይቅር የሚለው፣ እና የሚያድነው ስለ ስሙ ሲል እና ለራሱ ክብር ሲል መሆኑ አጽንኦት ሊሰጠው የሚገባው ለምንድን ነው? ብዙ ምክንያቶች አሉ፣ ለዛሬ ግን ሁለቱን እንመልከት።
1) እግዚአብሔር ሰዎችን የሚወደውና ይቅር የሚለው ለራሱ ክብር ሲል ነው ብለን አጽንኦት መስጠት ያለብን መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ በርካታ ቦታዎች ላይ እንደዚያ ስለሚል ነው።
ስለ ራሴ ስል መተላለፍህን የምደመስስልህ፣ እኔ፣ እኔው ነኝ፤ ኀጢአትህን አላስባትም። (ኢሳይያስ 43፥25)
እግዚአብሔር ሆይ፤ ኀጢአቴ ታላቅ ነውና፣ ስለ ስምህ ይቅር በልልኝ። (መዝሙር 25፥11)
አዳኛችን የሆንህ አምላክ ሆይ፤ ስለ ስምህ ክብር ብለህ ርዳን፤ ስለ ስምህ ስትል፣ ታደገን፤ ኀጢአታችንንም ይቅር በል። (መዝሙር 79፥9)
እግዚአብሔር ሆይ፤ ከአንተ መኰብለል አብዝተናል፤ በአንተም ላይ ዐምፀናል፤ ኀጢአታችን ቢመሰክርብንም እንኳ፣ ስለ ስምህ ብለህ አንድ ነገር አድርግልን። (ኤርምያስ 14፥7)
እግዚአብሔር ሆይ፤ ክፋታችንን ዐውቀናልና፤ የአባቶቻችንን በደል ተረድተናልና፤ በእርግጥም በአንተ ላይ ኀጢአት ሠርተናል። ስለ ስምህ ብለህ አትናቀን፤ የክብርህንም ዙፋን አታዋርድ። (ኤርምያስ 14፥20-21)
በደሙም በሆነው እምነት፣ እግዚአብሔር የማስተስረያ መሥዋዕት አድርጎ አቅርቦታል፤ ይህንም ያደረገው ቀድሞ የተፈጸመውን ኀጢአት ሳይቀጣ በትዕግሥት በማለፍ ጽድቁን ለማሳየት ነው፤ በአሁኑ ዘመን ይህን ያደረገው፣ ጽድቁን ይኸውም እርሱ ራሱ ጻድቅ ሆኖ፣ በኢየሱስ የሚያምነውን የሚያጸድቅ መሆኑን፣ ለማሳየት ነው። (ሮሜ 3፥25-26)
ኀጢአታችሁ ስለ ስሙ ተሰርዮላችኋልና። (1ኛ ዮሐንስ 2፥12)
2) እግዚአብሔር ሰዎችን የሚወደውና ይቅር የሚለው ለራሱ ክብር ሲል ነው ብለን አጽንኦት መስጠት ያለብን እግዚአብሔር ሊወድደን በሚችለው ታላቁ መውደድ እንደወደደን ስለሚያረጋግጥ ነው።
አባት ሆይ፤ እነዚህ የሰጠኸኝ፣ እኔ ባለሁበት እንዲሆኑ ዓለም ሳይፈጠር ስለ ወደድኸኝ የሰጠኸኝንም ክብሬን እንዲያዩ እፈልጋለሁ (ዮሐንስ 17፥24)።
እግዚአብሔር የሚወደን እኛን በሚያገን መንገድ ሳይሆን ራሱን በሚያገን መንገድ ነው። መንግስተ ሰማይ የራሳችንን ምስል በሚያንጸባርቁ መስታወቶች የተሞላ ስፍራ አይደለም። ነገር ግን እየጨመረ የሚመጣ ታላቅነት እና ልዕልና የሚታይበት ቦታ ነው። መንግስተ ሰማይ ደርሰን የራሳችንን ልቀት የምናይ ቢሆን ኖሮ፣ ያ የመጨረሻ አሳዛኝ ጉዳይ ይሆን ነበር።
ታላቁ የእግዚአብሔር ፍቅር እግዚአብሔር በሚያደርገው ነገር ሁሉ ገንኖ፣ ልቆ፣ ከፍ ብሎና ጎልቶ መታየቱን ያረጋግጣል። ስለዚህም መንግስተ ሰማያት በምንሄድበት ጊዜ ደስታችን የሚመሰረተው ለዘላለም በሚጨምር ነገር ላይ ነው፦ ይህም የእግዚአብሔር ክብር ነው። ሊደረስበት የማይቻለው ታላቁ ፍቅርም እግዚአብሔር በልጁ ሕይወት ዋጋ፣ ራሱን ለእኛ ዘላለማዊ ደስታ አድርጎ መስጠቱ ነው (ሮሜ 8፥32)። እግዚአብሔር ይወደናል ስለ ስሙም ሲል ይቅር ይለናል ሲል ይህን ማለቱ ነው።