ሊታሰብ የሚችለው ታላቁ መዳን | ታሕሳስ 21

እነሆ፥ ከእስራኤል ቤትና ከይሁዳ ቤት ጋር አዲስ ቃል ኪዳን የምገባበት ወራት ይመጣል፥ ይላል እግዚአብሔር።

ትንቢተ ኤርሚያስ 31፥31

እግዚአብሔር ቅዱስ እና ፍትሐዊ አምላክ ሲሆን፣ ከእንደኛ ዐይነት ኀጢአተኞች ፍጹም የተለየ ነው። በገናም ጊዜ ሆነ በዓመቱ የትኛውም ወቅት ዋና ችግር የሚሆንብን ነገር ይህ ነው። እጅግ ቅዱስ እና ፍጹም ፍትሐዊ ከሆነ አምላክ ጋር እንዴት እንታረቅ? ይህ በእንዲህ እንዳለ፤ እግዚአብሔር በምሕረት የተሞላ አምላክ ሲሆን፣ ክርስቶስ ከመወለዱ አምስት መቶ ዓመት በፊት፣ በትንቢተ ኤርሚያስ ምዕራፍ 31 አንድ ቀን አዲስን ነገር እንደሚያደርግ ይናገራል። ጥላዎቹን ሁሉ ዋነኛው በሆነው መሲሕ እንደሚተካ ቃል ይገባል። በታላቅ ኀይል በሕይወታችን ውስጥ እየሠራ ከውጭ የሚከለክለን ነገር ሳይኖር ከውስጣችን ፈቅደን እንድንወደው፣ እንድንታመነው እና እንድንከተለው ፈቃዱን በልባችን ይጽፋል።

ሊታሰብ የሚችለው ታላቁ መዳን ይህ ነው። እግዚአብሔር በአጽናፈ ዓለሙ ሁሉ ውስጥ ሊገኝ የሚችለውን ታላቁን እውነታ ሐሴት እንድናደርግበት በነፃ ሰጥቶናል። ከዚህም አልፎ፣ ይህንን እውነታ በታላቅ ነፃነት እና እርካታ እያጣጣምን እንድናውቀው ማድረጉ እጅግ ታላቅ ነገር ነው። ይህ እውነት ሊዘመርለት የሚገባ እጅግ ውድ የገና ስጦታ ነው። ይህንንም ነው በአዲሱ ኪዳን ቃል የገባው። ሆኖም ግን አንድ ታላቅ ዕንቅፋት ነበር። ያም ዕንቅፋት በኀጢአታችን እና በዐመፃችን ምክንያት ከእግዚአብሔር መነጠላችን ነው።

ቅዱስ እና ፍትሐዊ የሆነው ይህ አምላክ እኛን ኀጢአተኞችን እንዲህ ባለ ርኅራኄ ተመልክቶ፣ በአጽናፈ ዓለሙ ውስጥ ያለው ታላቁን እውነታ (ልጁን) ሐሴት እንድናደርግበት ሊሰጠን እንዴት ይችላል? መልሱ ደግሞ ይህ ነው። እግዚአብሔር ኀጢአታችንን ኢየሱስ ላይ በመጫን ፍርዱን ልጁ ላይ አደረገ፤ ቅድስናው እና ፍትሐዊነቱ ሳይዛባ በደላችንን ሊተውልን እና በምሕረቱ ሊገናኘን ስለፈለገ፣ በእኛ ምትክ ልጁ ላይ ፈረደበት። “ክርስቶስ የብዙ ሰዎችን ኀጢአት ለመሸከም፣ እንዲሁ አንድ ጊዜ መሥዋዕት ሆኖአል፤ ሁለተኛ ጊዜም ይገለጣል፤ ይህም ለሚጠባበቁት ድነትን ለማምጣት እንጂ ኀጢአትን ለመሸከም አይደለም” (ዕብራውያን 9፥28)።

ክርስቶስ በመስቀል ሲሞት በገዛ ሰውነቱ ውስጥ ኀጢአታችንን ተሸክሞ ነበር (1ኛ ጴጥሮስ 2፥24)። ለእኛ የተገባውን ፍርድ ወሰደልን (ሮሜ 8፥3)። በደላችንን ሰረዘልን (ሮሜ 8፥1)። ይህም ማለት ከእንግዲህ ኀጢአታችን ተወግዷል ማለት ነው (ሐዋርያት ሥራ 10፥43)። እግዚአብሔር ኀጢአታችንን በልቡ ቋጥሮ ሊከሰን ቀን እየጠበቀ አይደለም። ይህ ማለት በአንድ መልኩ ኀጢአታችንን ይረሳል ወይም አያስብብንም ማለት ነው (ኤርሚያስ 31፥34)። ኀጢአታችን ሁሉ በክርስቶስ ሞት ተቃጥሎ ከስሟል።

ይህ ማለት እግዚአብሔር አሁን ቃላት ሊገልጹት የማይችሉትን ታላቁን የአዲስ ኪዳን ተስፋ ቃል አትረፍርፎ ሊሰጠን ፍትሐዊ የሆነው ባሕርይው ይፈቅድለታል ማለት ነው። በአጽናፈ ዓለማችን ካሉት ተጨባጭ እውነታዎች ሁሉ የሚልቀውን ታላቁን እውነታ ኢየሱስ ክርስቶስን ደስታችን ይሆን ዘንድ ሰጠን። በሙሉ ልባችን፣ በነፃነት እና ያለ አንዳች መከልከል ክርስቶስን እንድንወድ እና እንድንገዛለት የገዛ ፈቃዱን፣ የልቡን መሻት በልባችን ላይ ጻፈልን።