ደስተኛው እግዚአብሔር | መስከረም 30

ይህ ጤናማ ትምህርት ቡሩክ (ደስተኛ) እግዚአብሔር ለእኔ በዐደራ ከሰጠኝ የክብር ወንጌል ጋር የሚስማማ ነው።” (1ኛ ጢሞቴዎስ 1፥10-11 – አጽንኦት ተሰጥቷል)

የእግዚአብሔር ክብር ትልቁ ክፍል ደስታው ነው።

ለጳውሎስ፣ እግዚአብሔር ዘላለማዊ ደስታ ሳይኖረው ዘላለማዊ ክብር አይኖረውም። ቡሩክ እግዚአብሔር መሆኑ፣ ለዘላለም ደስተኛ መሆኑን ያሳያል።

እግዚአብሔር ዘላለማዊ ደስታ የሌለው ነገር ግን ፍጹም የከበረ ነው ብሎ ማሰቡ ለጳውሎስ አዳጋች ነበር። ለዘላለም መክበር ማለት ለዘላለም ደስተኛ መሆን ነው። ጳውሎስ፣ “የደስተኛው (ቡሩክ) እግዚአብሔር ክብር” የሚለውን ሐረግ የተጠቀመው፣ ለዘላለም ደስተኛ መሆኑ በራሱ የከበረ ነገር ስለሆነ ነው።

የእግዚአብሔር ክብር ስንል፣ እርሱ እኛ ከምናስበው በላይ ደስተኛ መሆኑንም ያካትታል።

ወንጌል ይህ ነው፦ “የደስተኛው (ቡሩክ) እግዚአብሔር የክብር ወንጌል።” ይህ ከመጽሐፍ ቅዱስ የተጠቀሰ ጥቅስ ነው! እግዚአብሔር በከበረ መልኩ ደስተኛ መሆኑ መልካም ዜና ነው።

ማንም ሰው ደስተኛ ካልሆነ አምላክ ጋር ለዘላለም መኖር አይፈልግም። እግዚአብሔር ደስተኛ ካልሆነ፣ የወንጌሉ ግብ ደስ የሚያሰኝ ግብ አይደለም ማለት ነው። ይህ ማለት ደግሞ በጭራሽ ወንጌል አይደለም።

ነገር ግን ኢየሱስ ደስተኛ ከሆነው ከእግዚአብሔር ጋር ለዘላለም እንድንኖር እንዲህ እያለ ይጋብዘናል፦ “ወደ ጌታህ ደስታ ግባ” (ማቴዎስ 25፥23)። የኢየሱስ ደስታ (የእግዚአብሔር ደስታ) በእኛ እንዲሆንና ደስታችንም ሙሉ እንዲሆን ኖረ፤ ሞተም (ዮሐንስ 15፥1117፥13)። ስለዚህም ወንጌል “የደስተኛው (ቡሩክ) እግዚአብሔር የክብር ወንጌል” ነው።

የእግዚአብሔር ደስታ በዋነኝነት እና በቀደሚነት በልጁ ላይ ነው። ስለዚህ ከዚህ ደስታ ስንካፈል፣ አብ በልጁ የሚሰማውን ያንኑ ደስታ እየተካፈልን ነው ማለት ነው።

ለዚህ ነው ክርስቶስ አብን የገለጠልን። በዮሐንስ 17፥26 ጸሎቱን ሲጨርስ ለአባቱ እንዲህ ብሏል፦ “ለእኔ ያለህ ፍቅር በእነርሱ እንዲሆን፣ እኔም በእነርሱ እንድሆን፣ አንተን እንዲያውቁ አድርጌአለሁ፤ እንዲያውቁህም አደርጋለሁ።” ኢየሱስ እግዚአብሔርን የገለጠልን፣ አብ በወልድ ያለው ደስታ በእኛ ውስጥ እንዲኖር እና ደስታችንም በልጁ እንዲሆን ነው።