ሙሽራ በሙሽራዪቱ ደስ እንደሚለው፣ አምላክሽም በአንቺ ደስ ይለዋል። (ኢሳይያስ 62፥5)
እግዚአብሔር ለሕዝቡ መልካምን ሲያደርግ፣ አንድ ዳኛ ጥላቻና ፍርድ ለተገባው ወንጀለኛ ደግነትን በሚያሳይበት መንገድ አይደለም። ይልቁንም ሙሽራ ለሙሽራዪቱ ፍቅሩን በሚገልጥበት መንገድ ነው።
አንዳንድ ጊዜ፣ “የጫጉላ ጊዜ አልቋል” በማለት ስለ ጋብቻ እንቀልዳለን። ይህ ግን የሆነው እኛ ውስን ስለሆንን ነው። በጫጉላ ጊዜ ያለንን የፍቅር ግለት ማስቀጠል አንችልም። ነገር ግን እግዚአብሔር በሕዝቡ ያለው ደስታ፣ ሙሽራ በሙሽራዪቱ ደስ እንደሚለው ዓይነት እንደሆነ ይናገራል። ይህ ማለት ግን መጀመርያ አካባቢ የነበረው ፍቅርና ሞቅታ ከጊዜ በኋላ እየቀዘቀዘ ይሄዳል ማለቱ አይደለም።
እያወራ ያለው ስለ ጫጉላ ግለት፣ ስለ ጫጉላ ደስታዎች፣ ስለ ጫጉላ ጉልበት፣ ሐሴት እና ጉጉት ነው። በፍጹም ልቡ በእኛ ደስ እንደሚለው በሙሉ ልባችን እንድንረዳ ይፈልጋል። “ለእነርሱ መልካም በማድረግ ደስ ይለኛል፤ በፍጹም ልቤና በፍጹም ነፍሴ በእውነት በዚህች ምድር እተክላቸዋለሁ” (ኤርምያስ 32፥41)። “እግዚአብሔር አምላክሽ በመካከልሽ አለ፤ እርሱ ብርቱ ታዳጊ ነው፤ በአንቺ እጅግ ደስ ይለዋል፤ በፍቅሩ ያሳርፍሻል፤ በዝማሬም በአንቺ ላይ ከብሮ ደስ ይሰኛል” (ሶፎንያስ 3፥17)።
ከእግዚአብሔር ጋር የጫጉላ ጊዜ አያልቅም፣ ፍቅሩም አይበርድም። በኃይሉ፣ በጥበቡና በፈጠራ ችሎታው ወሰን የለሽ ስለሆነ፣ ለሚቀጥሉት ትሪሊዮን ዓመታት አንዳች መሰላቸት አይኖርም።