ስለ ክርስቶስ ስም ብትሰደቡ፣ የክብር መንፈስ የሆነው የእግዚአብሔር መንፈስ በእናንተ ላይ ስለሚያርፍ ብፁዓን ናችሁ። (1ኛ ጴጥሮስ 4፥14)
በዚህ ዘመን በዓለም ላይ የሚኖሩ ብዙ ክርስቲያኖች ክርስቶስን በማመን ምክንያት ሊመጣ የሚችልን ሕይወትን የማጣት አደጋ አያውቁትም። ከእንደዚህ ዓይነት ስደት ወጥትን በነፃነት መኖርን ተላምደናል። ትክክለኛው አካሄድ ይሄ ይመስለናል።
በዚህም ምክንያት፣ የመከራ ስጋት ሲኖርብን ወይም መከራ ሲያጋጥመን ቀዳሚው ምላሻችን ቁጣ ነው። ሆኖም ያ ቁጣ የሚያሳየው በዚህ ምድር መጻተኞች ሆነን እንደምንኖር መርሳታችንን ነው። “ወዳጆች ሆይ፤ በዚህ ዓለም እንግዶችና መጻተኞች እንደመሆናችሁ መጠን …” መባላችንን ዘንግተናል (1ኛ ጴጥሮስ 2፥11)።
ምናልባትም በዚህ ዓለም በጣም ተደላድለን ይሆናል። ጳውሎስ ይሰማው የነበረው የክርስቶስ ናፍቆት እኛን አይሰማን ይሆናል፦ “እኛ ግን አገራችን በሰማይ ነው፤ ከዚያ የሚመጣውንም አዳኝ፣ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን በናፍቆት እንጠባበቃለን” (ፊልጵስዩስ 3፥20)።
ብዙዎቻችን ማስታወሻ ያስፈልገናል፦ “ወዳጆች ሆይ፤ እንደ እሳት የሚፈትን ብርቱ መከራ በመቀበላችሁ እንግዳ ነገር እንደ ደረሰባችሁ በመቍጠር አትደነቁ” (1ኛ ጴጥሮስ 4፥12)። መከራ ለእውነተኛ አማኝ እንግዳ ነገር አይደለም።
በመጨረሻው የመከራ ሰዓት ምላሻችሁ ምን እንደሚሆን አስባችሁ ታውቃላችሁ? ባለጠመንጃው አነጣጥሮባችሁ “ክርስቲያን ነህ/ነሽ?” ብሎ ሲጠይቃችሁ ምን ትመልሱ ይሆን? አሁን ከምትገምቱት በላይ ምላሻቸሁ መልካም እንዲሆን ተስፋን የሚሰጣችሁ ብርቱ ቃል አለላችሁ።
ጴጥሮስ እንዲህ ይላል፦ “ስለ ክርስቶስ ስም ብትሰደቡ፣ የክብር መንፈስ የሆነው የእግዚአብሔር መንፈስ በእናንተ ላይ ስለሚያርፍ ብፁዓን ናችሁ” (1ኛ ጴጥሮስ 4፥14)። ይህ የጴጥሮስ ማበረታቻ የሚለን፣ ባልተለመደ መከራ ውስጥ (ስድብም ሆነ ሞት) “የክብር መንፈስ የሆነው የእግዚአብሔር መንፈስ በእኛ ላይ ያርፋል” ነው። ክርስቲያን በመሆናቸው መከራ ለሚደርስባቸው ሰዎች እግዚአብሔር በችግር ጊዜ ልዩ እርዳታ እንደሚሰጣቸው ይነግረናል።
ይህ ማለት ሌላ ዓይነት መከራን ስንቀበል እግዚአብሔር ከእኛ ጋር አይኖርም ማለት አይደለም። ጴጥሮስ ግን፣ “ስለ ክርስቶስ ስም” መከራን የሚቀበሉ ሰዎች ላይ ልዩ የሆነ “የክብርና የእግዚአብሔር መንፈስ” “ያርፍባቸዋል” በማለት አጽንኦት ይሰጣል።
ስለ ክርስቶስ ስም መከራ ወደ እናንተ በሚመጣበት ጊዜ እንዲሁ እንዲሆንላችሁ ጸልዩ። በሌላ ጊዜ የማይኖረን የጽናት ምንጭ እና የተትረፈረፈ ጸጋ ለዚህ ከባድ ጊዜ ይዘጋጅልናል። ስለዚህ በርቱ፣ አይዟችሁ።