“እሆንላታለሁ” ይላል እግዚአብሔር | ሕዳር 27

በውስጧ ካለው የሰውና የከብት ብዛት የተነሣ፣ ኢየሩሳሌም ቅጥር እንደሌላት ከተማ ትሆናለች፤ እኔ ራሴ በዙሪያዋ የእሳት ቅጥር እሆንላታለሁ፤’ ይላል እግዚአብሔር ‘በውስጧም ክብሯ እሆናለሁ።” (ዘካርያስ 2፥4-5)

በብዙ ድካም እና ተስፋ መቁረጥ ስሜት ከእንቅልፌ የምነሳባቸው ጊዜያት አሉ። ብዙ ጊዜ ግልጽ የሆነ ይሄ ነው የምለው ምክንያት የለኝም። በቃ እንዲያው የሆነ ነገር ሊበላሽ ነው፤ ጥፋቱም የእኔ ይሆናል የሚል ግራ የሚያጋባ ስሜት ነው።

አብዛኛውን ጊዜ እንደዚህ የሚሰማኝ የሆነ ሰው እኔን ወይም አገልግሎቴን ከተቸ በኋላ ነው። አንዳንዴ ደግሞ በፊቴ ከባድ ሥራ ኖሮ ቀነ ገደቡ ሲደርስብኝ፣ ወይም ደግሞ አልገፋ ሲለኝ እንዲህ ይሰማኛል።

ከ50 ዓመታት በላይ ያስቆጠሩትን እንዲህ ያሉ ማለዳዎችን መለስ ብዬ ሳስብ፣ ጌታ ኢየሱስ እንዴት ሕይወቴን እና አገልግሎቴን እንደጠበቀልኝ ያስገርመኛል። የሚያስደንቀኝ ነገር፣ ይህ ዐይነት ጭንቀት ይታገለኛል እንጂ አሸንፎኝ አያውቅም። ለዚህ ደግሞ ታላቁን አምላኬን አከብራለሁ።

በፍርሀት ሽባነት ውስጥ ተውጬ እንድቀር ከመፍቀድ ይልቅ፣ የእርዳታ ጩኸትን እንድጮህ በውስጤ ቀስቅሷል። ከዚያም እርግጥ በሆኑ ቃልኪዳኖቹ ጩኸቴን መልሷል።

አንድ ምሳሌ ላንሳ። ይህ የተከሰተው በቅርቡ ነበር። የደካማነት እና የመሸነፍ ስሜት እየተሰማኝ ከእንቅልፌ ነቃሁ። ዝያለሁ። ውስጤ ባዶ ሆኗል። እንደምንም ተጣጥሬ፣ “ጌታ ሆይ እርዳኝ፤ እንዴት መጸለይ እንዳለብኝ እንኳን ጠፍቶኛል” አልኩት።

ከአንድ ሰዓት በኋላ፣ ለለመንኩት እርዳታ መልስን ፍለጋ የዘካርያስን መጽሐፍ ማንበብ ጀመርኩ። እርዳታውም ያኔ መጣ።

“‘በውስጧ ካለው የሰውና የከብት ብዛት የተነሣ፣ ኢየሩሳሌም ቅጥር እንደሌላት ከተማ ትሆናለች፤ እኔ ራሴ በዙሪያዋ የእሳት ቅጥር እሆንላታለሁ፤’ ይላል እግዚአብሔር ‘በውስጧም ክብሯ እሆናለሁ’” (ዘካርያስ 2፥4-5)።

ለእግዚአብሔር ሕዝብ አስደናቂ ብልጽግና እና እድገት ስለሚኖር ኢየሩሳሌም ከአሁን በኋላ በቅጥር ውስጥ ተገድባ አትኖርም። “የሰውና የከብቶች ብዛት” እጅግ በጣም ብዙ ከመሆኑ የተነሣ ኢየሩሳሌም በምድሪቱ ላይ ያለቅጥር እንደተንሰራፉ ብዙ መንደሮች ትሆናለች።

እስራኤልን በተትረፈረፈ ብልጽግና የባረካት እግዚአብሔር ስለሚያደርግላት ጥበቃ ደግሞ እንዲህ ይላል፦ “እኔ ራሴ በዙሪያዋ የእሳት ቅጥር እሆንላታለሁ”። ይኸው ነው የተስፋው ቃል! እግዚአብሔር “እሆንላታለሁ” ሲል እንዲህ ነው። እኔም የሚያስፈልገኝ ይህ ነው። እግዚአብሔር ይሆንልኛል!

ይህ ቃል ኪዳን ባዷቸውን ለቀሩት የኢየሩሳሌም መንደሮች እውነት ከሆነ፣ የእግዚአብሔር ልጅ ለሆንኩት ለእኔም እውነት ነው። ለእግዚአብሔር ሕዝብ የተሰጡትን የብሉይ ኪዳንን ተስፋዎች የምተገብርበት መንገድ ይህ ነው። የተስፋ ቃሎቹ ሁሉ በክርስቶስ ለእኔ ናቸው (2ኛ ቆሮንቶስ 1፥20)። እግዚአብሔር በክርስቶስ ላሉት እያንዳንዱን ተስፋ እንዴት አብልጦ አይሰጥ? እግዚአብሔር በዙሪያዬ የእሳት ቅጥር ይሆንልኛል! አዎን ይሆናል። እስካሁንም ነበር፤ ወደፊትም ይሆናል።

በዚህ ብቻ አያበቃም። በዚያ የእሳት ቅጥር ውስጥ ተጨማሪ የሚሆንልኝ ነገር አለ። “በውስጧም ክብሯ እሆናለሁ” ብሏል። እግዚአብሔር የእሳቱን ጥበቃ በመስጠት ብቻ አያቆምም ፤ ዓላማው በእርሱ መገኘት ውስጥ ባለው ዘላቂ ደስታ ሊያረካን ነው። እግዚአብሔር ይሆንልኛል፤ እኔም እወድደዋለሁ!