“ሰዎች በእኔ ምክንያት ቢሰድቧችሁ፣ ቢያሳድዷችሁና ክፉውን ሁሉ በሐሰት ቢያስወሩባችሁ፤ ብፁዓን ናችሁ። በሰማይ የምትቀበሉት ዋጋ ታላቅ ስለ ሆነ ደስ ይበላችሁ፤ ሐሤት አድርጉ፤ ከእናንተ በፊት የነበሩትን ነቢያት እንደዚሁ አሳደዋቸዋልና።”(ማቴዎስ 5፥11–12)
በማቴዎስ 5፥44 ላይ ተመርኩዤ ጠላቶቻችንን ስለመውደድ በሰበኩኝ ጊዜ፣ ካቀረብኳቸው ጥያቄዎች ውስጥ አንዱ፦ የሚያግቷችሁን ከዚያም የሚገድሏችሁን ሰዎች እንዴት ነው የምትወዱት? የሚል ነበር።
ይህንን እንዴት ማድረግ እንችላለን? እንደዚህ ያለ የመውደድ ሃይልስ ከየት ይመጣል? እንዲህ ያለው ፍቅር በገሃዱ ዓለም ሲገለጥ ምን ያህል አስደናቂ ሊሆን እንደሚችል አስባችሁታል! የክርስቶስን እውነተኛነት፣ ኃይሉንና እውነታውን ከዚህ የበለጠ የሚያሳይ ነገር ይኖር ይሆን?
በማቴዎስ ወንጌል 5፥44 ላይ፣ ኢየሱስ አስደናቂና መስዋዕትነትን የሚጠይቅ ፍቅር እንዲኖረን የሚያስችለንን ዋና ቁልፍ ነገር ቀደም ብሎ በዚሁ ምዕራፍ ላይ እንደሰጠን አምናለሁ።
በማቴዎስ ወንጌል 5፥44 ላይ “ጠላቶቻችሁን ውደዱ ለሚያሳድዷችሁም ጸልዩ” ብሎ ስለ መሰደድ እንደተናገረው ሁሉ፣ በማቴዎስ 5፥11-12 ላይ በድጋሚ ስለ ስደት ያወራል። በእነዚህ ጥቅሶች ውስጥ የሚያስደንቀው ነገር ኢየሱስ የጠላትን በደል መቋቋም ትችላላቸሁ ብቻ አለማለቱ ነው። ይልቁንም በእርሱ ተደሰቱ ይለናል። “ሰዎች በእኔ ምክንያት ቢሰድቧችሁ፣ ቢያሳድዷችሁና ክፉውን ሁሉ በሐሰት ቢያስወሩባችሁ፤ ብፁዓን ናችሁ። . . . ደስ ይበላችሁ፤ ሐሴትም አድርጉ።”
ይህ ለጠላቶቻችን ከመጸለይ ወይም ለእነርሱ መልካምን ከማድረግ የበለጠ የማይቻል ነገር ይመስላል። ታዲያ ይህን በሰው አቅም የማይቻል ነገር ካደረኩ፣ ማለትም በመሰደዴ ከተደሰትኩ፣ ያን ጊዜ አሳዳጆቼን መውደድ እችላለሁ ማለት ነው። በፍትህ መጓደል፣ በስቃይና በኪሳራ ፍርሃት መካከል የደስታ ተአምር መከሰት ከቻለ፣ ታዲያ በደሉን ለፈጸሙትም ወንጀለኞች የፍቅር ተአምር መከሰት ይችላል ማለት ነው።
ኢየሱስ በእነዚህ ጥቅሶች ውስጥ የደስታን ቁልፍ ሰጥቶናል። “በሰማይ የምትቀበሉት ዋጋ ታላቅ ስለ ሆነ ደስ ይበላችሁ፤ ሐሤት አድርጉ” ብሎናል። ታዲያማ የደስታው ቁልፍ በእግዚአብሔር የወደፊት ጸጋ ላይ ያለ እምነት ነው። ማለትም፣ እግዚአብሔር ለእናንተ ይሆንላችኋል ብሎ ቃል በገባው ነገር ሁሉ እርካታ ማግኘት ማለት ነው። “በሰማይ የምትቀበሉት ዋጋ ታላቅ ስለ ሆነ ደስ ይበላችሁ” ይላል። በስደት ውስጥ የሚኖረን ደስታ ወዳለንበት አስፈሪ ጊዜ ተመልክቶ ጠላታችንን መውደድ እንድንችል ነጻ የሚያወጣን ከሰማይ የሚፈስ ደስታ ነው። ስለዚህ፣ ይህ ደስታ ጠላቶቻችን ሲያሳድዱን፣ እኛ ግን እነርሱን መውደድ እንድንችል ነፃ የሚያወጣን ኃይል ነው።
ይህ እውነት ከሆነ ታዲያ፣ የፍቅር ትእዛዝ በውስጥ ታዋቂነት አእምሯችንን በላይ ባሉት ነገሮች ላይ — ማለትም በምድር ባሉት ነገሮች ላይ ሳይሆን እግዚአብሔር ለእኛ እንደሚሆን ቃል በገባልን ነገሮች ላይ — እንድናደርግ የተሰጠ ትእዛዝ ነው ማለት ነው (ቈላስይስ 3፥2)።
ጠላታችንን የመውደድ ትእዛዝ ተስፋችንንና ጥልቅ የሆነውን የነፍሳችንን እርካታ በእግዚአብሔር እና በታላቅ ሽልማቱ፣ ማለትም በወደፊቱ ጸጋው ላይ እንድናደርግ የተሰጠ ትእዛዝ ነው ማለት ነው። የዚህ አስደናቂ ፍቅር ቁልፍ በእግዚአብሔር የወደፊት ጸጋ ላይ ያለ እምነት ነው። በመከራችንና በጭንቀታችን መካከል፣ የእግዚአብሔር ፍቅር “ከሕይወት ይበልጣልና” የሚለውን እውነት ልናምን ይገባናል (መዝሙር 63፥3)። ጠላቶቻችሁን መውደድ የመንግስተ ሰማያትን ዋጋ አያስገኝላችሁም። የመንግስተ ሰማያትን ዋጋ እንደ ውድ ሀብታችሁ መቁጠራችሁ ግን ጠላታችሁን እንድትወዱ ኃይልን ይሰጣችኋል።